ምሥጢረ ቀንዲል (ቅብዓ ሕሙማን)


ምሥጢረ ቀንዲል (ቅብዓ ሕሙማን)

“ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።” (ጄምስ 5:14).

ምሥጢረ ቀንዲል ሰዎች በሥጋ በታመሙ ጊዜ ብርታትና ኃይል እንዲያገኙ፣ እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲያደርግላቸውና በመንፈስ ጠንክረው እንዲቆሙ የሚሰጥ ቅዱስ ቅባት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በሥጋችን ስንታመም የድካም፣ የፍርሃትና የጭንቀት ስሜት ይሰማናል፡፡ ስለዚህ ካህን መጥቶ ብርቱዎች እንድንሆን ይጸልይልናል፤ በቅዱስ ቅባትም እየቀባ ያጽናናል፡፡

እግዚአብሔር “ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎአል (ዘጸ 15፡ 26)፤ ምሥጢረ ቀንዲል ማለት በጠና ሕመም ላይ ለሚገኘው ሰው ፈዋሽ ወደሆነው እግዚአብሔር መጸለይና ቅዱስ ዘይት መቀባት ነው፡፡    ካህኑ እየጸለየ ሕመምተኛውን የሚቀባው ቅዱስ ቅባት የፈውስ፣ የብርታትና የእግዚአብሔር ልጅና ወዳጅ መሆኑን የሚያስገነዝብ ምልክት ነው፡፡ ሕመምተኛው ውስጣዊ ሰላምና ፈውስ እንዲያገኝ የሚያደርግ ነው፡፡

ምሥጢረ ቀንዲል ለታመመው ሰው በእግዚአብሔር እንዲተማመን፣ ተስፋ እንዲያደርግና የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚወርስ የሚያረጋግጥለት ነው፡፡ ወደ መጨረሻው ቤት ለሚደረገው ጉዞ ዝግጁ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ 

ምሥጢረ ቀንዲል የታመመውን ሰው የክርስቶስ ሕማም ተካፋይ መሆኑን የሚያስገነዝበው ነው፡፡ በመሆኑም በሥጋው የሚያሠቃየውን ጊዜያዊውን ሕመም አምኖ እንዲቀበልና የክርስቶስን መስቀል እያየ በጽናት እንዲጓዝ የሚያደርገው ነው፡፡

ሕመምተኛው ቀድሞውኑ በምሥጢረ ንስሓ ያልተሠረየለት ኃጢአት መኖሩን ከተረዳና ከተሰማው፣ በምሥጢረ ቀንዲል ጸሎተ ሥርዓት የጸጸት መንፈስ ካሳየ ኃጢአቱ ይሰረይለታል፤ ነፍሱ ትጨነቅበት ከነበረው የኃጢአት ሰንሰለት ተፈትታ ነፃ ትሆናለች፡፡ ስለዚህ ምሥጢረ ቀንዲል ለሕሙማን የሚሰጠው ሥቃይ ከተሞላበት ሕይወት ለመዳን ብቻ ሳይሆን የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘትና በዘላለማዊ ሕይወት ተካፋይ ለመሆንም ጭምር ነው፡፡ 

ነቢዩ አስቀድሞ “እኛ ልንሸከመው የሚገባንን መከራና ሕማም እርሱ ተሸከመ” በማለት ስለ ክርስቶስ ተናገረ (ኢሳ 53፡ 4)፤ ክርስቶስ ደግሞ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” በማለት ፈዋሽ መሆኑን ተናገረ(ማቴ 8፡ 7)፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ዛሬም የሕመማችን ተካፋይ ይሆናል፤ በምሥጢራት አማካይነት እንድንፈወስ ይረዳናል፡፡ ስንጨነቅና በፍርሃት ስንዋጥ ብርቱዎች ሆነን፣ የተረጋጋ መንፈስ ተላብሰን መስቀላችንን በትዕግሥት ተሸክመን እንድንጓዝ ያደርገናል፡፡               

ምሥጢረ ቀንዲል (ቅብዓ ሕሙማን) እንዴት ተመሠረተ?

ጌታ ኢየሱስ የታመሙትን በእጆቹ እየዳሰሰና እየጸለየ የፈወሰበት ጊዜ ብዙ ነው (ማር 15፡ 29-31፤ ሉቃ 5፡ 13)፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ወደ እርሱ ይጥራ፤ እነርሱም በሽተኛውን በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት” ይላል(ያዕ 5፡ 14)፡፡

ደቀ መዛሙርትም ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሰዎችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ (ማር 6፡ 13)፡፡ ስለዚህ ስለታመሙት መጸለይና ዘይት እየቀቡ ኃይልና ብርታት እንዲያገኝ ማድረጉ ከአዲስ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ሲደረግ የነበረ ተግባር ነው፡፡

ደጉ ሳምራዊ በመንገድ ተደብድቦ ወደ ወደቀው ወደ ምስኪኑ ሰው ቀርቦ ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሉ ላይ አፈሰሰ፤ በጨርቅም ጠምጥሞ አሠረለት (ሉቃ 10፡ 34)፡፡ ይህ የሚያሳየው የታመመን ሰው በመርዳት ሂደት ዘይት ትልቅ ቦታ እንደነበረው ነው፡፡ በጸሎት መንፈስና በሙሉ እምነት ሕመምተኛው የሚቀባው ቅዱስ ዘይት ደግሞ ኃይል የሚያላብሰው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በምሥጢረ ቀንዲል የሚሰጠው ዘይት ደግሞ “ቅዱስ ቅባት” ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “በሽተኞችን ፈውሱ፣ ሙታንን አስነሡ፣ ለምጻሞችን አንጹ፣ አጋንንትን አስወጡ፣ በነፃ የተቀበላችሁትን በነፃ ስጡ” ብሎ ተናገራቸው (ማቴ 10፡ 8)፡፡ “ታምሜ ጎብኝታችሁኛል” በማለት ሕሙማን መጐብኘት እንዳለባቸውና ለሕሙማን ልዩ ትኩረት እንደነበረው ተናግሮአል(ማቴ 25፡ 36)፡፡ በዚህ መሠረት የታመሙት ይፈወሱ ዘንድ ይጸለይላቸዋል፤ በቅዱስ ቅባትም ይቀባሉ፤ ልዩ ጸጋ ይቀዳጃሉ፡፡

ምሥጢረ ቀንዲል (ቅብዓ ሕሙማን) መቀበል የሚችል ማን ነው?

በሕመም ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት መኝታ ላይ የሚገኝ ማንኛውም ክርስቲያን በአቅራቢያው የሚገኝ ካህን አስጠርቶ እንዲጸለይለትና ቅዱስ ቅባት እንዲሰጠው ማድረግ ይችላል፡፡ የታመመው ሰው ካህን ለመጥራት በማይችልበት ሁኔታ ላይ ሲገኝ በአቅራቢያው የሚገኘው ሰው ይህንን በማድረግ ሊተባበረው ይገባል፡፡

ቅብዓ ቅዱስ በተለያየ ጊዜ ደጋግሞ መቀበል ይቻላል፤ ይህም መጀመሪያ የተቀበለው ሕመምተኛ ከዳነ በኋላ በድጋሚ ቢታመም ይህንን ምሥጢር እንዲሰጠው ደግሞ መጠየቅ ይችላል፡፡ 


በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።