ምሥጢረ ተክሊል
ምሥጢረ ተክሊል
ምሥጢረ ተክሊል አንድ ወንድና አንዲት ሴት በክርስትና እምነት ተጠምቀው፣ በእግዚአብሔር ፈቃድና በራሳቸው ነፃ ፍላጎት ሙሉ ስምምነት አድርገውና ተፈቃቅደው፣ ተገቢውን የመንፈስና የዕውቀት ዝግጅት ካጠናቀቁ በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር የሚፈጽሙት ቃል ኪዳን ነው፡፡
ምሥጢረ ተክሊል ሁለት የነበሩ ሰዎች አንድ የሚሆኑበት፣ “እኔ” ማለትን ትተው “እኛ” በሚል መልክ መኖር የሚጀምሩበትና በደግም ሆነ በክፉ ዘመን ሳይለያዩ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ለመጓዝ ቃል በመገባባት የሚኖሩት ምሥጢር ነው፡፡
ምሥጢረ ተክሊል ሁለት ተጋቢዎች በመንፈስና በአሳብ አንድ ሆነው፣ የእግዚአብሔር ጸጋ ተላብሰው፣ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በእግዚአብሔር ጥላና ከለላ ሥር መኖር እንዲችሉ የሚፈጽሙት መንፈሳዊ የውል ስምምነት ነው፡፡ ስምምነቱም ከእግዚአብሔር ጋር ሲሆን ካህን እና ሌሎች ምስክሮች በተገኙበት በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ምሥጢር ነው፡፡
ምሥጢረ ተክሊል ሰዎች በሰብአዊነታቸው ያላቸውን ልዩነት ወደ ጐን በመተው፣ ለጋራ ጥቅምና ጥሩ የሆነ ቤተሰብ ለመመሥረት ተፈቃቅረውና ተቻችለው በአንድነት እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ እንዲኖሩ የሚያደርግ ምሥጢር ነው፡፡
ጋብቻ በመጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት እንዴት ይገለጻል?
ብሉይ ኪዳን
እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክና አምሳያ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ ምድርን ይሙላ፤ ምድርም በቁጥጥራችሁ ሥር ትሁን በማለት ባረካቸው (ዘፍ 1፡ 27-28)፡፡ ይህ በረከት የሚያሳየው የወንድና የሴት አንድነትና ውሕደት ገና ጥንት በእግዚአብሔር የታቀደና የተፈቀደ እንደሆነ ነው፡፡ በእርግጥ ጋብቻ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ቅዱስ የሆነ የሕይወት ክፍል ነው፡፡ ገና ከዓለም አፈጣጠር ታሪክ ጋር ጋብቻ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር እና ሕይወቱን እንዳካፈለ የምንረዳበት መንገድ ነው፡፡
በዘፍጥረት መሠረት የጋብቻ ሕይወት ሰው የብቸኝነትን ኑሮ በመተው፣ ትዳር መሥርቶ፣ እርስ በርስ ተስማምቶ፣ ተጋግዞና ተረዳድቶ ለመኖር የተሠራ ምሥጢር ነው (ዘፍ 2፡ 23)፡፡ የጋብቻ ሕይወት ገና ከፍጥረት መጀመሪያ በእግዚአሔር የተቀደሰ፣ ሁለት የተለያዩ ሰዎችን አንድ አድርጎ የሚያኖርና ጽኑ የሆነ ውሕደት የሚፈጥር፣ ወንድና ሴት ከወላጆቻቸው በመለየት ሳይተፋፈሩ የራሳቸውን ሕይወት መሥርተው የሚኖሩበት ምሥጢር ነው(ዘፍ 2፡ 24-25)፡፡
እግዚአብሔር ለጋብቻ ሕይወት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠውና እንደሚባርከው ከአብርሃምና ከሣራ፣ ከይስሐቅና ከርብቃ፣ ከያዕቆብና ከራሔል የጋብቻ ሕይወት አኗኗር መረዳት እንችላለን፡፡ የወንድና የሴት ጋብቻ የአንድነት ሕይወት የሚገለጽበት፣ ይቅርታ የሚዘወተርበት፣ ምሕረት የሚደረግበት፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊፈርስ የማይችል የቃል ኪዳን ምሥጢር እንደሆነ በነቢያት ተነግሮአል፡፡ ነቢያት ይህንን ለማስገንዘብ የእስራኤልና የእግዚአብሔር ግኑኝነት በመጠቀም በተደጋጋሚ በተለያየ መልኩ ተናግረዋል (ሆሴ 3፤ ኤር 3፡ 14)፡፡
እግዚአብሔር የጋብቻ ሕይወት የተከበረ፣ ለሁል ጊዜ የሚኖር ሕይወት እንደሆነና ፍቺ እንደሚጠላ በነቢዩ ሚልክያስ አማካይነት ተናግሮአል (ሚል 2፡ 16)፡፡
ከአንድ ሚስት በላይ በማግባታቸው ምክንያት ብዙ ችግር እንደገጠማቸው ከንጉሥ ዳዊትና ከንጉሥ ሰለሞን ሕይወት መረዳት እንችላለን (2 ሳሙ 12፤ 1ነገ 11) ፡፡ እግዚአብሔር ጋብቻን በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ቅዱስ የሆነ የሕይወት ክፍል አድርጎ ሠራው፤ ቀጥሎም “አታመንዝር” እንዲሁም “የሌላውን ሚስት አትመኝ” በማለት ግልጽ የሆነ ትእዛዝ ሰጠ(ዘጸ 20፡ 14፡ 17)፡፡
አዲስ ኪዳን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ቃና በሠርግ ግብዣ ላይ በመገኘትና ጋብቻውንም በመባረክ የጋብቻን ክቡርነት አረጋገጠ (ዮሐ 2)፡፡ ወንድና ሴት በጋብቻ ሕይወት ውስጥ አንድ ሆነው ይኖራሉ፤ እግዚአብሔር ያጣመራቸው ሰው አይለያቸውም በማለት ጌታችን ኢየሱስ አረጋግጦአል(ማር 10፡ 9፤ ማቴ 19፡ 1-12)፡፡
የጋብቻ ሕይወት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን የጠበቀ ወዳጅነትና አንድነት የሚያንጸባርቅበት ምሥጢር ነው (ኤፌ 5፡ 22-23)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ሁሌም ይወዳታል፤ ይንከባከባታል፤ ይመራታል፤ ወዳጅነቱና ውሕደቱ በምንም መልኩ አይቀየርም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የባልና የሚስት ሕይወትም ሊፈርስ በማይችል ሁኔታ ተሳስሮ ይኖራል፡፡
ጋብቻ ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ተከባብረውና ተደጋግፈው የሚኖሩበት ምሥጢር እንደሆነ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይገልጻል (1ጴጥ 3፡ 1-7)፡፡ ጋብቻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሕብረትና ውሕደት ፈጥረው፣ አንድ ቤት መሥርተውና በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አጥብበው የሚኖሩበት ምሥጢር ነው (1ቆሮ 11፡ 11)፡፡
እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አገላለጽ የጋብቻ ሕይወት ሰው ራሱን በሥነ ምግባር አንጾ፣ ከኃጢአት ራሱን ጠብቆ፣ ቤተሰብ መሥርቶ፣ በመተሳሰብና በመረዳዳት ለመኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ የሕይወት ክፍል ነው፡፡ ይህንንም ሲያረጋግጥ “በዝሙት ኃጢአት ላለመውደቅ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት የራስዋ ባል ይኑራት” ይላል (1ቆሮ 7፡ 2)፡፡
የጋብቻ ሕይወት ውስጥ ወንድና ሴት በውይይት፣ በመረዳዳትና አንዱ የሌላውን ተገቢውን መብት በመጠበቅ የሚኖር ምሥጢር ነው(1ቆሮ 7፡ 3)፡፡ እርስ በርሳቸው በአንድነት የሚኖሩትና በምንም ምክንያት ሳይለያዩ አብረው የሚጓዙት ምሥጢር ነው(1ቆሮ 7፡ 10-11)፡፡
የጋብቻ ሕይወት ትልቅ ኃላፊነት የተሞላ ሕይወት ነው፤ ኃላፊነቱም በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ዘወትር የትዳር አጋርን ማስደሰት፣ በማንኛውም ውሳኔዎች የትዳር ወዳጅን ማሰብና ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ነው (1ቆሮ 7፡ 32-33)፡፡ በተጨማሪም ልጅ ወልዶ በጥሩ ሥነ ምግባር ማሳደግ(1ቆሮ 7፡ 14)፣ የኑሮ ችግሮችን በትዕግሥትና በጥረት መወጣት የሚጠይቅ ነው(1ቆሮ 7፡ 28)፡፡
የጋብቻ ሕይወት እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ታማኝ ሆኖ መኖርን የሚጠይቅ ነው (1ቆሮ 7፡ 39)፡፡ በእርግጥ ከሁለቱ የትዳር ጓደኞች አንዱ በሞት ቢለይ ሌላው ደግሞ ነፃ ይሆናል፤ በመሆኑም እምነቱን ጠብቆ ከአንድ የክርስትና እምነት ተከታይ ጋር ዳግመኛ ትዳር ሊመሠርትም ይችላል(1ቆሮ 7፡ 39)፡፡
የጋብቻ ዋና ዋና ዓላማዎች የትኞቹ ናቸው?
1. እርስ በርስ ተፈቃቅሮ፣ ውሕደት ፈጥሮ፣ በአንድ ቤት ውስጥ እየተረዳዱና እየተሳሰቡ ለመኖር ነው፡፡ የጋብቻ ዋና ዓላማው ወንድና ሴት ሙሉነትን ፈጥረው በፍቅር ለመኖር ነው፡፡ ጋብቻ አንዱ ለሌላው ራስን መስጠት ስለሚጠይቅ አንዱ ራሱን በፍቅር ለሌላው ይሰጣል፤ በፍቅር መኖርን ይማራል፡፡ እርስ በርሳቸው ተፈቃቅረው ሲኖሩ የእግዚአብሔር ፍቅር ታማኝ ምስክሮች መሆናቸውን ይገልጻሉ፤ በፍቅር ሲዋሐዱ ሙልአትን ይፈጥራሉ፡፡
ልጅ ወልዶ በኃላፊነት ለማሳደግ፣ ለማስተማርና በመልካም ሥነ ምግባር ለማነጽ ነው፡፡ በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ልጅ መውለድ ብቻ በቂ አይደለም፤ ዋናውና ትልቁ ነገር የወለዱት ልጅ መንከባከብና ማስተማር ነው፡፡ ምንም እንኳ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እግዚአብሔር ቢሆንም ወላጆች ልጅ ወልደው በኃላፊነት በጥሩ ሥነ ምግባር ሲያሳድጉ ከፈጣሪ ጋር ይተባበራሉ፤ በእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ ተካፋዮች ይሆናሉ፡፡
ሌላው የጋብቻ ዓላማ ጥሩ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ነው፡፡ አንድ ቤተሰብ በጥሩ ሥነ ምግባር ከታነጸና ሰላማዊ መንፈስ ተላብሶ የሚኖር ከሆነ ጥሩ የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ፈሪሃ እግዚአብሔር የተላበሰና በጥሩ ሥነ ምግባር ታንጾ የሚኖር ቤተሰብ እንደ አንድ ጸሎት ቤት ይቈጠራል፡፡ በመሆኑም ጋብቻ ለማኅበረሰብ ዕድገት፣ ለሰላማዊ ሕይወት፣ ጥሩ ዜጋ ለማፍራት፣ በሥነ ምግባራዊ ሕይወት ራስን አንጾ ለመኖር የሚረዳ ወሳኝ የሆነ የሕይወት ክፍል ነው፡፡
ጋብቻ ራስን ከኃጢአት ፈተና ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አንድ ሰው ብቻውን የሚኖር ከሆነ በዝሙት ኃጢአት ሊፈተን ይችላል፤ ስለዚህ በምኞት ፈተናም ሆነ በተግባር ወደ ዝሙት በሚወስደው ፈተና ላለመውደቅ ጋብቻ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል (1ቆሮ 7፡ 2)፡፡
የእግዚአብሔር ፍቅር የበለጠ ለመረዳትና በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ ይጠቅማል፡፡ አንዲት ክርስቲያን ሴት ክርስቲያን ያልሆነ ባል ልታገባ ብታስብ እርሱን ወደ እግዚአብሔር ፍቅርና ወደ ደኅንነት መንገድ መምራት ይኖርባታል፡፡ እርሱ የሚድንበት መንገድ ማሳየት ይገባታል፡፡ ወንዱም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ትዳራቸው ከመግባታቸው በፊት ክርስቲያን ያልሆነች ሴት ሊያገባ ቢያስብ የእርስዋ ነፍስ የሚድንበት መንገድ ማሳየት አለበት (1ቆሮ 7፡ 15-16)፡፡
ቃል ኪዳን ፈጻሚዎች ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ አለባቸው?
ሁለቱ ተጋቢዎች ሙሉ ፈቃደኞች መሆናቸውን፣ ያለምንም ወይም ያለማንም ተጽእኖ የሚጋቡ መሆኑን ለቤተ ክርስቲያን ማሳወቅ፣ ቀጥሎም የጋብቻ ዝግጅት ትምህርት መማርና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡
ከጤንነትም ሆነ ከሥጋዊ ዝምድና ወይም ከእምነት አኳያ አንዱ ወገን ለሌላው ወገን የሚደብቀው ምንም ዓይነት ምሥጢር መኖር የለበትም፡፡ በዝግጅት ጊዜ በግልጽ ተነጋግረው በሚገባ መተዋወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የጤንነት ችግርም ካለ መወያየት ይኖርባቸዋል፡፡
ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አኗኗር ጋር በተያያዘ ያሉ ሁኔታዎች በሙሉ ሁለቱ ተጋቢዎች አስቀድመው መነጋገርና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሁለቱ አንዱ ከካቶሊክ እምነት ሳይሆን ከሌላ የክርስትና እምነት ተከታዮች የመጣ ወይም የመጣች ከሆነ አስቀድሞ ለቆሞሱ አሳውቆ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከሁለቱ አንዱ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መሠረት ለመኖር ዝግጁ ካልሆነ ወይም ካልሆነች አስቀድሞ በአቅራቢያው ካለው ቆሞስ ጋር መነጋገር፣ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና አስፈላጊ የሆነ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል፤ ከቆሞሱ ጋር በመነጋገር ቤተ ክርስቲያን ስለምትፈቅዳቸው አማራጮች መወያየት ይገባል፡፡
ለቃል ኪዳን ሥርዓት የሚዘጋጁት የጋብቻ ዝግጅት ትምህርት ከሚያስተምሩዋቸው ቆሞስ ጋር አስፈላጊውን ስምምነት ቢያደርጉም ከእምነት አኳያ ተጋቢዎቹ ልጆቻቸውን በካቶሊክ እምነት ለማሳደግ መስማማት አለባቸው፤ ይህም በዝግጅት ወቅት መታወቅ ይኖርበታል፡፡
የቃል ኪዳን ቀለበት ትርጓሜ ምንድን ነው?
ቃል ኪዳን በሚፈጸምበት ዕለት የሚባረከውና በጣቶቻቸው የሚያጠልቁት ቀለበት የታማኝነት ምልክት ነው። ከዚያን ሰዓት ጀምሮ አንዱ ለሌላው ታማኝ፣ ቃል ኪዳኑን ላቆመለት እግዚአብሔር ታማኝ፣ ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ እንዲሁም በዕለቱ በጸሎት ላጀበው ሕዝብ ታማኝ ሆነው እንደሚኖሩ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ እንደሆነና ሁሌም ከእርስዋ እንደማይለይ ሁሉ የትዳር አጋር የሆኑትም እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አይለያዩም፤ በመሆኑም በጣታቸው አጥልቀውት በሚኖሩት ቀለበት ምሳሌነት አንዱ ሌላውን በልቡ ውስጥ በፍቅር ይዞት እንደሚኖር የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡
ቀለበት ዙሪያው ክብ እንደሆነ ሁሉ አንዱ በሌላው ፍቅር ታጥሮና ተከልሎ እንደሚኖር የሚያሳይ ውጫዊ ምልክት ነው፡፡ በቃል ኪዳን ዕለት ቀለበቱ ተባርኮ አንዱ በሌላው ጣት ላይ ሲያጠልቀው “በአንተ ወይም በአንቺ የፍቅር ክልል ውስጥ ብቻ በታማኝነት እንደምኖር ቃል እገባለሁ” እንደማለቱ ነው፡፡
ትዳር ሳይመሠርቱ መኖር ይቻላልን?
በምንኩስና ሕይወት እግዚአብሔርን እያገለገሉ ለመኖር ውሳኔ የሚያደርጉ ሰዎች ትዳር ላይመሠርቱ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ለመንግሥተ ሰማይ ብለው ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው የሰጡ ናቸው (ማቴ 19፡ 12)፡፡ እነርሱ ትዳር ይዞ ከሚኖረው ከማንኛውም አማኝ በላይ በሙሉ አሳባቸው እግዚአብሔርን ብቻ እያገለገሉ መኖርን ስለሚፈልጉ ትዳር አይመሠርቱም(1ቆሮ 7፡ 34-37)፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው ሚስት ያላገባ ሰው ጌታ ኢየሱስ የሚደሰትበትን ነገር ስለሚፈልግ አሳቡ የሚያተኩረው ጌታ ኢየሱስን በሚመለከት ሥራ ነው (1ቆሮ 7፡ 32)፡፡ በመሆኑም ሙሉ ጊዜውን፣ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ሕይወቱን ለእግዚአብሔር መስጠት ስለሚኖርበት ትዳር ባይኖረው አገልግሎቱ የበለጠ ይሆናል፡፡
ላላገቡና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች “ሳያገቡ እንደ እኔ ቢኖሩ መልካም ነው” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የራሱን የአገልግሎት ሕይወት ምሳሌ በማድረግ ይናገራል (1ቆሮ 7፡7)፡፡ በእርግጥ ትዳር መሥርቶም እግዚአብሔርን ማገልገል ቢቻልም ትዳር ያልመሠረተው ግን በአገልግሎት ሕይወቱ ውስጥ የተሻለ ያደርጋል
በሚስጥረ ተክሊል ጋብቻ ለመፈፀም የሚያስቡ ከሆነ፤ ለበለጠ መረጃ ሠርጉን ለማድረግ ከታሰበበት ቀን አንድ ዓመት ያህል ቀደም ብለው በስልክ ቁጥር 647 995-8606 ወይም በ ኢሜል አድራሻችን lmethiocatholic@gmail.com ይጠይቁን።
በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።