የልጆች እና የወጣቶች

አንተ ጐበዝ፥ በጕብዝናህ ደስ ይበልህ፥ በጕብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፥ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ፤ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ።
— መጽሐፈ መክብብ - ምዕራፍ 11:9

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በቶሮንቶ ከምትሠራቸው ሥራዎች አንዱና መሠረታዊው የሆነው ሕፃናትንና ወጣቶችን በካቶሊካዊ እምነታቸው ማጎልበትና ጠንካራ ክርስቲያኖች እና ዘላቂ የክርስትያን ቤተሰብና ማሕበረሰብ አባላት እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው፡፡

ካቶሊክ ወይም ክርስቲያን መሆን ምን ማለት እንደሆነና የካቶሊክን እምነትንና ባህሉን ከማስተማር ባሻገር፡ ቤተክርስቲያንዋ የሕጻናቱንና የወጣቶቹን በእራስ መተማመን ለማጠንከር ይረዳቸው ዘንድ በተለያዩ የቤተክርስቲያን ግልጋሎቶች ውስጥ እንዲሳተፉ ታደርጋለች። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል በሳምንታዊ ዕለተ እሁድ ቅዳሴ ጊዜ መጽሓፍ ቅዱስ ንባባትን እንዲያነቡ፤ መዝሙሮች፤ መንፈሳዊ ድራማዎች እንዲያዘጋጁ እና የመሳሰሉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ታግዛለች/ታበረታታለች፡፡

በተጨማሪም በተለያየ የዕድሜ ክልል በመከፋፈልና የሚያስፈልጋቸውን ጊዜና ቦታ በማዘጋጀት በእግዚአብሔር ፀጋ እንደየ አቅማቸው ካቶሊካዊ ሥርዓትን የተከተለ የጋራ ፀሎት እንዲጸልዩ፣ እርስ በእርስ ዉይይት እንዲያደርጉ፣ መንፈሳዊ ትምህርቶችን እንዲማማሩና በእምነታቸው የጸኑና በቅድስና የታነጹ የካቶሊክ ቤተሰብ ሆነው እንዲያድጉ ታግዛቸዋለች፡፡

እርስዎም ልጆችዎን በዚህ የወጣቶችና የህጻንት ዝግጅት ውስጥ ማሳተፍ ከፈለጉ የዝግጅቱን አስተባባሪ መላከሰላም አየለ በስልክ ቁጥር 416-836-7435 ወይም lmethiocatholic@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።

 

የቀጣዩን ትውልድ እምነት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ሥርዓት ማነፅ 

የካቶሊክዊት ክርስትና እምነት መሠረታዊው መርህ እርስ በእርሳችን፣እንዲሁም በህይወታችን ዘመን ከምናገኛቸው ጋር ሁሉ በፍቅር፣ በበጎነት እና ቸርነትን በማሳየት መኖር ነው። 

ለዚህ ክርስቲያናዊ ፀጋ ታማኝ እንድንሆን፤ የደብሩ ምዕመናን በየዕለቱ ህይወታችን ሁሉን ቻይ ወደሆነው ወደ አምላካችን በመፀለይ እና የእመቤታችን የቅድስት ማርያም እና የቅዱሳን አማላጅነት እንዳይለየን ተግተን እንማለዳለን፣እንጸልያለን፡፡

ልጆቻችንም በዚህ ክርስቲያናዊ ፀጋ ተኮትኩተው እንዲያድጉ እንሻለን:: ቤተክርስቲያናችንም በእግዚአብሔር ፀጋና በረከት ተሞልተን፣ በክርስትና ህይወት ታንጸን እንድንኖር ትረዳናለች። የቤተክርስትያን ምስጢራትን፣ የክርስቶስ እና የሐዋርያቶችን ወንጌልና አስተምሮዎችንም ትመግበናለች፡፡ 

በእድሜ የተቸረና የበለፀገ ልዩ እና ቱባ ወግና ባህል ያዳበረው የግዕዝ ኢትዬጵያዊ ካቶሊካዊ እምነትና ሥርዓት ሁላችንም የምንሳሳለትን ወንድማዊ ህብረት እንድንጠብቅ አግዞናል:: የአዛውንቶች፣ የወላጆች፣ የወጣቶችና የህፃናት ተሳትፎና የህብረት ፀሎትም ለረጅም ዘመን የህይወታችን ዋና መልህቅ ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተተላልፎልናል:: በፀሎት፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ እና የቤተክርስትያን ምስጢራትን በመቀበል የምናገኘው ፀጋ እና በኢትዮዽያዊ ካቶሊካዊ መዝሙሮች መደሰት የሚገኘው ሁሉም ትውልድ በክርስቶስ አንድነትና በወንድማማችነት ስንኖር ነው:: 

የፍቅር ብርሃን እና ቸርነት በእኛ ህይወት ብቻ ሳይወሰን በወቅቱ አብረውን ላሉት ልጆቻችንና ለቀጣዩ ትውልድ እንደበራ ለማስተላለፍ የሚጠበቅብንን ግዴታ ለመወጣት ይረዳን ዘንድ እግዚአብሔር ፀጋውን እንዲሰጠን እንፀልያለን። የእግዚአብሔርም ፈቃድ እኛ ክርስቶስ ባስተማረን መንገድ እንድንራመድ፥ ቀጣዩ ትውልድም በእዚሁ መንገድ እንዲቆይ ማሳየት እና በመጨረሻም ትንሳኤንና ዘላለማዊ ህይወትን መጠበቅ እንዳለብን መረዳት ነው። በኢትዮዽያ ካቶሊካዊ እምነትና ልማድ የተቀበልነው በረከት ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲሻገር እንፀልያለን:: ልጆቻችንም ከወላጆቻቸው የሚተላለፈላቸውን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ እምነትና ሥርዓት ለሚቀጥለው ትውልድ በማስተላለፍ እምነቱና ወጉ እንዲበለፅግ የድርሻቸውን እስተዋፀኦ ያበረክታሉ።

እንደ ምዕምናን መንፈሳዊ አገልግሎት ማግኘት የጀመርነው እ.ኤ.አ በ 1990ዎቹ ዓ.ም. አጋማሽ ቢሆንም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተክርስቲያችን በምትመግበን ፍቅር ህብረታችን እና አንድነታችን ጸንቷል:: ለልጆቻችንም መልካም አርአያ ሆነናል:: በአባ ኢሳይያስ ፍጹም ፍቅርና አባታዊ መሪነት ልጆቻችን ወርሃዊ መስዋዕተ ቅዳሴ በእንግሊዘኛ እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን ለቤተሰብ የተለየ የቅዳሴ ፕሮግራም ይኖረናል:: 

ልጆቻችን ለእምነታቸው እውነተኛ እንዲሆኑ እና እርስ በእርስ በመተባበር እንዲደሰቱ ለማድርግ ደከመኝ ሰለቸኝን ለማያውቁት ለበጎ ፈቃደኛ የሰንበት ትምህርት አገልጋዮች ምስጋና ይገባቸዋል። 

የትውልድ ቅብብሎሽ ፈተናዎችም ሌሎች እህት አብያተ ክርስቲያናት ካለፉበት ጋር ተመሳሳይ ነው:: ዛሬ ልጆች ሲጎለምሱ በህይወት ውጣ ውረድ እና በስጋዊ ምኞት የሚፈተኑበት ጊዜ ነው:: በአካባቢያችን በምንኖርበት ማህበረሰብ አንዳንዶች የገጠማቸውን ፈተና በወሳኝነት አልፈው የትውልድ ቅብብል ማድረጋቸውን አይተናል:: እኛም ፈተናውን ከተሻገሩት ልምድ መቅሰም እንችላለን። ከሌሎች “ፍልሰተኛ ማኅበረሰቦች” ስህተት ተምረን እና ከስኬታቸውም ልምድ ቀስመን የኢትዮዽያ-ካናዳ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ህብረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና የስደተኛ ትውልዶችን መሻት እንዲያሟላ ጥረታችንን በእጥፍ ማሳደግ ይገባናል:: 

የቋንቋ እንቅፋት እና የባህል ልዩነትን ለመቅረፍ፣ የህፃናት እና የወጣቶችን ህይወት ለመታደግ ይረዳን ዘንድ፡ በማደግ ላይ ያለችው ቁምስናችን የዓላማ ጽናትና አንድነት ፣ተጨማሪ የቋንቋ እና የባህል ፕሮግራም ማዘጋጀት፣ ጠንካራ እምነትና ፀሎት ከሁሉም ወላጆች ይጠበቃል።

የእግዚአብሔር ፀጋ ይብዛልን!