ታሪካችን

የልደታ ማርያም ቤተክርስትያን በቶሮንቶ አጭር ታሪክ

በቶሮንቶ የሚገኙ ካቶሊክ ኢትዮጵያዊያን ለመጀመሪያ ጊዜ የቅዳሴ እና ቅዱስ ቁርባን አከባበር ስርዓት ለማድረግ ሙከራ ያደረግነው በአባ ግሩም ተስፋዬ እና በአገልጋይ ተሰማ ኅይለእየሱስ አማካይነት  በ1980ዎቹ ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር። ከዚያም በኋላ እስከ መስከረም 1995 ዓ.ም ድረስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህንኑ ስናደርግ ቆይተን ነበር፡፡

በመስከረም 1995 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በቶሮንቶ ሃገረ ሰብከት ፈቃድና እርዳታ አባ አሰፋ ተስፋይ በቶሮንቶ ለሚገኙ ካቶሊክ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን በቅዱስ ኒኮላስ ቤተከርስትያን እንዲያገለግሉ ተመደበው እስከ 1998 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ ሲያገለገሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚያም ከ1998 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ አባ ኤርሚያስ ገብረእግዚአብሄር ግልጋሎቱን በሴንት ክሌር ቤተክርስቲያን ቀጥለዋል፡፡

በቶሮንቶ የሚገኙ ካቶሊክ ኢትዮጵያውያን ማሕበረሰብ በአማርኛ ራሱን የቻለ ሥረዓተ ቅዳሴ እና መንፈሳዊ አገለግሎት ለማግኘት ብዙ ጥረት ሰያደረግ የቆየ ሲሆን፡ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ እየተሰበሰበ በጋራ ጸሎት በማድረግና በተገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ከተለያዩ ቦታዎች በሚመጡ ካህናት የሚመራ የቅዳሴ ሥርዓት ሲካፈል ቆይቷል፡ ከ2007 ዓ.ም  እስከ 2008 ዓ.ም. ባለው ጊዜ አባ ቪቶሪዮ ቦሪያ አልፎ አልፎ እዚሁ ቶሮንቶ ከተማ ውስጥ በምትገኘው በእመቤታችን ሉርድ ቤተከርስቲያን ውስጥ ካቶሊክ ኢትዮጵያዊያንን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ ምክር እና እርዳታ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብፅዑ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እና በቶሮንቶ ካርዲናል ቶማስ ኮሊንስ ስምምነት እና ቡራኬ አማርኛ ተናጋሪ ካህን እንዲመደብ እና የኢትዮጵያዊ ካቶሊካዊት ቤተከርስቲያን ሥርዓት፤ ባህል እና ቋንቋን የተከተለ መደበኛ ቅዳሴ እና መንፈሳዊ አገልገሎት እንዲሰጥ ተወሰነ። በዚሁም ውሳኔ መሰረት አባ ኢሳይያስ ዱላ ይህችን ቤተክርስትያን ለመመስረት የመጀመሪያው ካህን ሆነው ወደ ቶሮንቶ ተመድበው መጡ።

በ2009 ዓ.ም. በአባ ኢሳይያስ ዱላ መሪነትና በካቶሊክ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ተሳተፎ የተመሰረተችው ልደታ ማርያም ኢትዮጲያዊት ካቶሊካዊት ቤተከርስቲያን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቶሮንቶ እና በአካባቢው ለሚገኙ ካቶሊክ ኢትዮጵያውያን መደበኛ ቅዳሴ እና የተሟላ መንፈሳዊ አገልገሎት በቅድስት ማርያም ፖሊሽ ካቶሊካዊት ቤተከርስቲያን እየሰጠች ሲሆን፤ ቤተክርስቲያናችን በቶሮንቶ እና በአካባቢው ለሚኖሩ ካቶሊክ ኢትዮጵያዊያን የጋራ የመንፈሳዊ እና ማህበራዊ መሰብሰቢያ ቤት በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡