ምሥጢረ ንስሓ
ምሥጢረ ንስሓ
ንስሓ ማለት ቀድሞ አቅጣጫውን የሳተውን ሰው ከተጓዘበት የጥፋት መንገድ መመለስ ነው፡፡ የሚመለሰውም በመንፈስ ቅዱስ እገዛ አማካይነት ሙሉ የሆነ የልቦና ለውጥ በማድረግ፣ ውስጣዊ ሕይወቱን በማደስና በመለወጥ ዳግመኛ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ለመኖር ዕርቅ በማድረግ ነው፡፡
ከ 1፡30-2፡30 PM ባለው ጊዜ ሲሆን ከዚህ ውጪ በሌላ ቀን ማድረግ ከፈለጉ ካህኑን በስልክ ቁጥር
647-995-8606 ደውለው ቀጠሮ መያዝ ይችላሉ።
ንስሓ ከራስ ኅሊና፣ ከቤተ ክርስቲያንና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው፤ በመሆኑም ንስሓ “የእርቅ ምሥጢር” ወይም “የይቅርታ ምሥጢር” ተብሎ ይጠራል፡፡
ንስሓ ማለት ሰው በሕይወቱ መሰናክል የሆኑ ነገሮችን በማስተዋል አይቶ፣ ኅሊናውን አንጽቶ ከቀድሞው ጉድፍ ታጥቦ፣ በአዲስ መንፈስ፣ አዲስ ሕይወት ለመምራት መወሰን ነው፡፡ ንስሓ ማለት የቀድሞውን ሁሉ ምንም ሳይስቀሩ ተናዝዞ፣ ከታሰሩበት የኃጢአት ሰንሰለት ነፃ በመሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት መላበስ ማለት ነው፡፡
ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው በኃጢአት ሲወድቅ ኅሊናው ይወቅሰዋል፤ መንፈስ ቅዱስም ስለ ኃጢአቱ ይናገረዋል (ዮሐ 16፡ 8)፤ እግዚአብሔርም ያንን ሰው ንስሓ እንዲገባ ይናገረዋል(ራእ 2፡ 5፡ 16፤ 3፡ 19)፡፡ ኃጢአተኛው ንስሓ እንዲገባ እግዚአብሔር በቂ ጊዜ ይሰጠዋል(ሐዋ 11፡ 18፤ 17፡ 30፤ 2ጴጥ 3፡ 9)፡፡
ንስሓ በኃጢአት የተዘጋውን ልብ መልሶ መክፈት፣ የታወረውን ልቦና መልሶ ማብራት፣ ከኃጢአት ሞት መነሣት፣ ሕይወትን ማደስ ማለት ነው(ዮሐ 3፡ 3-8፤ 2ቆሮ 5፡ 17፤ ኤፌ 2፡ 10፤ 2ቆሮ 4፡ 4-6፤ ዮሐ 5፡ 20)፡፡
ንስሓ ኃጢአተኛው ሰው ምሕረት የሚያገኝበት መንገድ ነው፤ ኃጢአተኛው ንስሓ ሲገባ ደግሞ በሰማይ መላእክት ይደሰታሉ (ሉቃ 15፡ 10-32)፤ በአንጻሩ ሰዎች ከንስሓ ርቀው በእልኸኛነት መኖርን ሲመርጡ በኃጢአታቸው ምክንያት ይጠፋሉ(ሉቃ 13፡ 1-5)፡፡
ኃጢአት አንድ ሰው ለመኖር ካሰበው መልካም ሕይወትና ለመጓዝ ከሚፈልገው መልካም መንገድ በመውጣት አቅጣጫውን ወይም ዓላማውን ስቶ በተሳሳተ መንገድ መሄድ ነው፡፡ ኃጢአት የእግዚአብሔር ጸጋ መራቆትን፣ በመንፈስ መጐሳቈልን፣ ውስጣዊ ባዶነትንና መንፈሳዊ እርካታ ማጣትን ያስከትላል፡፡
ኃጢአት የኅሊና ጭንቀትና ውስጣዊ ሰላም ማጣትን ያስከትላል፡፡ ኃጢአት ከራስ ኅሊና፣ ከቤተ ክርስቲያንና ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው፤ ቀድሞ የነበረውን የልጅነት መንፈስና ክብር ማጣትና በውርደት መመላለስ ማለት ነው፡፡
ንስሓ ከኃጢአት ጋር ተባብሮ መኖርን እንደምንጠላ የምናሳይበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ አጥብቀን እንደምንፈልግ የምንገልጽበት መንገድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ተብለን በጸጋ ተሞልተን መኖር እንደምንፈልግ የምንመሰክርበት ሂደት ነው፡፡ ንስሓ ኃጢአተኞችን ሊፈልግ ወደመጣው ኢየሱስ መቅረብና የተገፈፍነውን ጸጋ ተላብሰን ከመንጋው ጋር በድጋሚ መቀላቀል ነው (ሉቃ 5፡ 31-32)፡፡ በእርግጥ ኢየሱስ የመጣው የጠፋውን ሊያድንና ሊፈልግ ነው(ሉቃ 19፡ 10)፡፡
ንስሓ ሰው በራሱ ፈቃድ ኅሊናውን ከመረመረ በኋላ ራሱን በመክሰስ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ምሕረትና ሰላም የሚቀዳጅበት፤ ያለፈውን የሚረሳበት፤ የወደፊቱን ተጠንቅቆ የሚኖርበት ምሥጢር ነው፡፡
የንስሓ ምሥጢር የተመሠረተው መቼ ነው?
የንስሓ ምሥጢር የተመሠረተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ “አብ እኔን እንደላከኝ እኔም ደግሞ እናንተን እልካችኋለሁ፤ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ ኃጢአታቸው ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” ባላቸው ጊዜ ነው (ዮሐ 20፡ 21-23)፡፡ በተጨማሪም ለጴጥሮስ “እነሆ ለአንተ የመንግሥተ ሰማይ ቁልፍ እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል” ብሎ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን በሰጠው ጊዜ ነው(ማቴ 16፡ 18-20)፡፡
በእርግጥ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ቢሆን እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ንስሓ ይጠራ ነበር፡፡ ነቢያት ሕዝቡን ወደ ንስሓ እየጠሩ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቅ ይቀሰቅሱና ያስተምሩ ነበር(ኢሳ 1፡ 16-31፤ ኢዩ 2፡ 12-17፤ ዮና 3)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስም ሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአገልግሎት ሥራቸውን ሲጀምሩ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚለውን የንስሓ ጥሪ በማሰማት ነበር(ማቴ 4፡ 17፤ ማር 1፡ 5፤ ማር 1፡ 14-15)፡፡
የንስሓ አደራረግ
1. ኅሊናን መመርመር
በንስሓ ጉዞ ላይ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት ባደረገ መልኩ ትሕትና ተላብሶ ኅሊናን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የኅሊና ምርመራ የሚደረገውም ዐሥርቱ ትእዛዛትን እንዴት እንደኖርናቸው፣ የትኞቹን እንደጣስንና እንዳፈረስን አንድ በአንድ እየቈጠርን በጥንቃቄ በመመርመር ነው (ዘጸ 20፤ ዘዳ 5)፡፡ ኢየሱስ ያስተማረው “የተራራው ስብከት” እንዴት እንደኖርናቸውና እየኖርናቸው እንደሆነም ጊዜ ወስዶ በጸጥታና በጽሞና በማሰብ ኅሊናን መመርመር ያስፈልጋል(ማቴ 5፡ 1-12)፡፡
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን ትእዛዛት በመባል የሚታወቁትን ማክበር አለማክበራችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ኅሊናን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ደግሞ እያንዳንዳችን በክርስትናም ሆነ በአገልግሎት ሕይወታችን ውስጥ በተግባር እንድንኖራቸው ቃል ገብተን ጉዞ ከጀመርን በኋላ ያፈረስናቸው ወይም ያልጠበቅናቸው ወይም ያልኖርናቸው ነገሮች ካሉ ከንስሓ በፊት ኅሊናን መመርመር ይገባል፡፡
በአጠቃላይአውቀንበድፍረትየሠራናቸውእንዲሁምበደንብሳንረዳበስሕተትየፈጸምናቸውንድክመቶቻችንሁሉበማስተዋልኅሊናችንመርምረንፊትለፊትማስቀመጥይገባል፡፡መጽሐፈ ምሳሌ “የሰውኅሊናየእግዚአብሔርመብራትስለሆነውስጣዊሰውነታችንሁሉይመረምራል” ይላል (ምሳ 20፡ 27)፡፡
2. መጸጸት
የቀድሞው ጉዞ የተሳሳተ እንደነበረ በመረዳት ዳግመኛ ወደ አፍቃሪው አባት ለመመለስ በሠሩት ስሕተት መጸጸት ይገባል፡፡ የቀድሞው አካሄዴ የተሳሳተ ነበር፤ በሰብአዊነቴ ስሕተት ሠርቻለሁ፤ በዚህም የእግዚአብሔር ጸጋ ጎድሎብኛል ብሎ መቀበል ያስፈልጋል፡፡
“ሰው ነኝና በሰብአዊነቴ ተሳስቼ ነበር” ብሎ ስሕተትን አምኖ መቀበል የብስለትና የጥሩ ክርስትና ሕይወት ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ንስሓ ከማምራት በፊት በሙሉ ልቦና፣ ትሕትና ተላብሶ መቅረብ ይገባል (ሉቃ 15፡ 17-19)፡፡ ስንቀርብም ቀድሞ የተጓዝነውን የሕይወት ጉዞ የተሳሳተ እንደነበር አምኖ በመቀበል ብቻ ሳይሆን በማዘንና በመጸጸት ነው፡፡
3. የሠሩትን ኃጢአት በሙሉ ለካህን መናዘዝ
ካህን እንደ አስታራቂና አገናኝ ድልድይ ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ የተቀመጠ መንፈሳዊ አባት ነው፤ የንስሓ አባት ነው፡፡ ኃጢአተኛው በተጸጸተና ባዘነ መንፈስ ትሕትና ተላብሶ ኃጢአቱን በሙሉ ለካህን ሲናገር ነፃነት ይሰማዋል፤ መንፈሱ ይረካል፤ እፎይታን ያገኛል፡፡ ስለዚህ የተረዳናቸውና በኅሊናችን ኃጢአት መስለው የተሰሙን በሙሉ ምንም ሳናስቀር ለካህን እንናገራለን፡፡
ካህንኃጢአተኛውንያደምጣል፤ይመክራል፤ይገሥጻል፤ስለኃጢአተኛውይጸልያል፤ከእግዚአብሔርናከቤተክርስቲያንጋርመታረቁንያውጃል (ሉቃ 17፡ 14)፡፡ካህንያደመጠውንየተናዛዡንኃጢአትበእግዚአብሔርፊትትቶከማናዘዣውቦታይወጣል፤ስላደመጠውኃጢአትናስለኃጢአተኛውዳግመኛአያስብም፤የሰማውንኃጢአትበምንምመልኩለሌሎችአይናገርም፡፡
4. ቁርጥ ፈቃድ ማድረግ
ኃጢአተኛው ተጸጽቶ ንስሓ ሲገባ ዳግመኛ ተመሳሳይ ኃጢአት እንደማይሠራና ቀድሞ ወደነበረበት ውድቀት እንደማይመለስ ለራሱ ቃል ይገባል፡፡ “ዳግመኛ እንደ ቀድሞው የኃጢአት ሕይወት አልኖርም” በማለት ወስኖ በአዲስ መንገድ ለመጓዝ ይነሣል፡፡ በዚያ ሰዓት የሚደረገው ኑዛዜ ልክ እንደ መጨረሻው ኑዛዜ መሆን ይገባዋል፡፡
መቼም ሰው ፍጹም ሆኖ በዚህ ምድር አይኖርም፤ ቢሆንም ግን ዛሬ ውስጣዊው ሕይወቱ በንስሓ ስለሚታጠብ ዳግመኛ እንዳይቆሽሽ የተቻለውን ሁሉ ተጋድሎ በማድረግ እንደሚኖር ለራሱና ለእግዚአብሔር ቃል ይገባል፤ ውሳኔ ያደርጋል፡፡
5. የኃጢአት ቀኖና (ካሳ) መፈጸም
ንስሓ የጸሎት ሕይወት ያስከትላል፤ በሚገባ ከተናዘዙና የካህኑን ምክር ካደመጡ በኋላ መጸለይና የተሰበረውን ልብ መጠገን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አናዛዡ ካህን ለተናዛዡ ሰው የተለያየ ዓይነት ጸሎት እንዲያደርግና የተለያዩ መንፈሳዊ ተግባራት እንዲያከናውን ስለሚያዙት ተናዛዡ በጥንቃቄ መፈጸም ይኖርበታል፡፡
የኃጢአት ቀኖና ወይም የኃጢአት ካሳ ከሚባሉት ለምሳሌ ዘወትር ጸሎት እንዲያደርግ፣ ቅዱስ ቁርባን እንዲያዘወትር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወትር እንዲያነብና እንዲያስተነትን፣ ድኾችን እንዲረዳ፣ ከሰዎች ጋር እንዲታረቅና እንዲያስታርቅ፣ የኅሊና ምርመራ ዘወትር እንዲያደርግ ሊመክሩት ይችላል፡፡ በመሆኑም ተናዛዡ የኃጢአት ካሣ እንዲሆን በአናዛዡ ካህን ፈጽም የተባለውን ሁሉ ምንም ሳያስቀር ማከናወን ይገባዋል፡፡
ለምን በካህን መናዘዝ አስፈለገ?
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ “በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” በማለት የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ሰጥቶታል (ማቴ 16፡ 19)፡፡ ጴጥሮስ የሐዋርያት ተወካይ በመሆን ቤተ ክርስቲያንን የመምራት ትልቅ ኃላፊነት ከኢየሱስ ተቀብሎአል(ማቴ 16፡ 18)፡፡
ቤተ ክርስቲያን የተቀበለችውን ተልእኮ ለካህናት ትሰጣለች፤ ካህናት የተመረጡና የተቀቡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ስለሆኑ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ይወጣሉ፡፡ ተልእኮውም ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ድልድይ መሆን ነው፡፡ እግዚአብሔር መሐሪ እንደሆነ ለኃጢአተኞች መንገዱን ማሳየትና የምሕረት መሣሪያ መሆን ነው፡፡
ካህን አስተማሪና ቀዳሽ ብቻ ሳይሆን አዋጅ ነጋሪም ጭምር ነው፡፡ አንድ ኃጢአተኛ ንስሓ ሲገባ ከቤተ ክርስቲያንና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቁን ያውጃል፡፡ ኢየሱስ ዐሥሩን ለምጻሞች “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” ያላቸው ምክንያት ስለነበረው ነው (ሉቃ 17፡ 14)፤ ምክንያቱም መፈወሳቸው፣ ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀላቸውና የእግዚአብሔር ምሕረት አግኝተው ወደ ጌታ መመለሳቸው ካህን ስለሚውጅላቸዋው ነው፡፡ በተጨማሪም ያደመጠውን ኃጢአት ምሥጢራዊነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ስለ ኃጢአተኛው ይጸልያል፡፡
ካህን የክርስቶስን ክህነት ሁለት ጊዜ ስለሚካፈል ነው፡፡ ይህም በመጀመሪያ በምሥጢረ ጥምቀት የንጉሥነት፣ የክህነትና የነቢይነት ጸጋ እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ይቀበላል፡፡ ቀጥሎም የአገልግሎት ክህነት ሲቀበል በሚቀባው ቅዱስ ዘይት አማካይነት ዳግመኛ የክርስቶስ ክህነት ተካፋይ ይሆናል፡፡
አናዛዡ ካህን ክርስቶስን ወክሎ ስለሚቀመጥ ርኅራኄ የተላበሰ፣ ታጋሽ፣ ምሕረት የተሞላና ተናዛዡን ወደ እግዚአብሔር ፍቅር የሚመራ ነው፡፡ ካህኑ ሁሌም ማናዘዣ ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ “በእኔ ቦታ ላይ አሁን ክርስቶስ ቢቀመጥ ለዚህ ኃጢአተኛ ተናዛዥ ምን ምላሽ ይሰጠው ነበር?” ብሎ እያሰበ የእግዚአብሔር ምሕረት ለተናዛዡ እንዲደርስ በተለያየ መልኩ መንገዱን ሁሉ ያመቻቻል፡፡
ካህን እግዚአብሔር መሐሪና፣ አፍቃሪ አባት እንዲሁም ኃጢአተኞችን ተቀብሎ በቤቱ ዳግመኛ የሚቀበል ሩኅሩኅ አባት መሆኑን የሚመሰክር ነው፡፡ ካህን ንስሓ ለማስገባት ሲቀመጥ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን የሚቀበልበትን በር የከፈተ መሆኑን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ነው፡፡
ካህን ራሱም ኃጢአት ስለሚሠራ ንስሓ ይገባል፤ ግን ምንም ኃጢአተኛ ቢሆንም እንኳ ያስታርቃል፤ የእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ተናዛዡ እንዲያልፍ ምክንያት ይሆናል፡፡ አንድ መሬት ውስጥ የተቀበረ የውሃ ማስተላለፍያ ቧንቧ ምንም እንኳ ከውጭ በኩል ቢቆሽሽም በውስጡ ንጹሕ ውሃ ማስተላለፉ አይቀርም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረው ልምድ ሲታይ አይሁዳውያን የእግዚአብሔር ምሕረት ሲፈልጉ ወደ ካህናት ዘንድ ሄደው ኃጢአታቸውን የተናዘዙበት ጊዜ እንደነበር እንረዳለን (ባሮ 1፡ 13)፡፡ ሕዝቡ ወደ ካህናት ዘንድ ሄደው የሚናዘዙትም ካህናት ለእግዚአብሔር ቅርብ ናቸው፤ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ተወካዮች ናቸው፤ በመሆኑም እግዚአብሔር ኃጢአታችን ይቅር እንዲልልንና ምሕረት እንዲያደርግልን ካህናት ድልድይ ሆነው ይረዱናል በሚል መልክ ነበር፡፡
ንስሓ የሚገባ ሰው የሚያገኘው በረከት ምንድን ነው?
ንስሓ ዘወትር ስለ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንድናስብ ያደርገናል፤ ከበደላችን የነጻን መሆናችንን ያረጋግጥልናል (2 ቆሮ 7፡ 11)፤ በኃጢአት ለተወጋው ነፍስ ፈውስ ያስገኝለታል፡፡ በንስሓ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልናል፤ ያጣነውን የልጅነት ክብር ያስገኝልናል፤ ዳግመኛ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ልጆች ሆነን ለመኖር እንድንችል ጸጋውን ያለብሰናል(ሉቃ 15፡ 20)፡፡
በንስሓ ምሥጢር መታጠብ ዘላለማዊውን ሕይወት እያሰብንና እየተመኘን እንድንኖር ያደርገናል፤ በቅድስና መንገድ እንድንመላለስና የሕይወት እንጀራ የሆነውን ክርስቶስን ዘወትር በሙሉ ልብ ለመቀበል ይረዳናል፡፡ ንስሓ የሥጋን ሞት እንዳንፈራና ማንኛውም ነገር ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡ ንስሓ መግባት የሚያዘወትር ሰው ድንገት ቢሞት እንኳ የሚያስጨንቀው ወይም የሚያስፈራው ነገር አይኖርም፡፡
ንስሓ የሚገባው መቼና በምን ጊዜ ነው?
ንስሓ የምንገባው ኃጢአት በሠራን ቁጥር ነው፡፡ ኅሊናችንን መርምረን በልባችን ውስጥ ኃጢአት መስሎ የሚሰማን ነገር መኖሩን በተረዳንበት ጊዜ ሁሉ ንስሓ በመግባት ከኅሊናችን፣ ከእግዚአብሔር፣ ከቤተ ክርስቲያንና ከሁሉም ወንድሞቻችን ጋር መታረቅ ይጠበቅብናል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔር ጸጋ ጎድሎአቸዋል” ይላል (ሮሜ 3፡ 23)፡፡ ስለዚህ ሁሌም ንስሓ እየገባን፣ በኃጢአት ምክንያት የጐደለንን ጸጋ አድሰንና ተላብሰን፣ በእግዚአብሔር ምሕረት ተጎብኝተን እንድንኖር ተጠርተናል፡፡ በዚህ መልኩ ሕያው የሆነውን የሕይወት እንጀራ ቅዱስ ቁርባንን ስንቀበል ሕይወታችን ይለመልማል፡፡
በተለያየ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ከሚገኝበት ስፍራ ርቀን የምንኖር ከሆንን ግን ግዴታ በታላላቅ በዓላት ወቅት ማለትም በክርስቶስ ልደትና ትንሣኤ ጊዜ በሚገባ ተናዝዘን መቁረብ ይኖርብናል፡፡
ካህን በንስሓ ጊዜ መፍታት የማይችለው ኃጢአት የትኛውን ነው?
አንድ ካህን ክርስቶስን ወክሎ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ በንስሓ ቦታ ይቀመጣል፡፡ ካህን የተናዛዡን ሁሉንም ኃጢአት ይሰማል፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ መመሪያና ደንብ መሠረት ካህኑ መፍታት የማይችላቸው ውስብስብ ነገሮች ካሉ ወደ ጳጳሱ ያስተላልፋል፡፡
አንድ ውርጃ የፈጸመ ሰው ወይም በውርጃ ሒደት የተሳተፈ ሰው ያደረገው ስሕተት እጅግ በጣም ከባድና የሕይወት ጉዳይ መሆኑን የበለጠ ይረዳ ዘንድ ወደ ሀገረስብከቱ ጳጳስ እንዲሄድ ካህኑ ይመክረዋል፤ ያበረታታዋል፡፡ ተናዛዡ ወደ ጳጳስ ለመሄድ ፈቃደኛ ካልሆነ ግን አናዛዡ ካህን ስለ ተናዛዡ ሄዶ ጳጳሱን ያማክራል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ካህን ሁሉንም ኃጢአት የመስማት፣ ተናዛዡን የመምከር፣ የማጽናናትና ወደ ዕርቅ መንገድ የመምራት ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሀገረስብከቱ ጳጳስ ለካህኑ ሁሉንም ኃጢአት ማለትም ውርጃንም ሆነ ሌሎች የሰውን ሕይወት የሚመለከቱ ከበባድ ኃጢአቶችን በተመለከተ ካህኑ ራሱ እዛው የንስሓ ቦታ ላይ እንዲጨርስ ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ካህኑ ተናዛዡን መክሮ፣ ገሥጾና የኃጢአት ካሳ ቀኖና ሰጥቶ መሸኘት ይችላል፡፡
በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።