ቅዱስ ቁርባን
ቅዱስ ቁርባን
ቅዱስ ቁርባን በኅብስትና በወይን መልክ ተዘጋጅቶ፣ በቅዳሴ ጸሎት ውስጥ በምሥጢራዊ ሂደት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ተለውጦ፣ በንስሓ ታጥበውና ተዘጋጅተው በእምነት ለሚቀበሉት የሚሰጥ የነፍሳችን ምግብ ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን መንፈሳዊ ሕይወታችን የሚያለመልምና የሚያጠነክር የሕይወት እንጀራ ነው፡፡
ቁርባን የሚለው ቃል “ኧካሪስቶ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተተረጐመ ነው፡፡ በግሪክ “ኧካሪስቶ” ማለት “ማመስገን” ወይም “የምሥጋና መሥዋዕት ማቅረብ” እንደማለት ነው፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበት ምሽት ከሐዋርያት ጋር የመጨረሻው ራት ሲበሉ እንጀራን አንሥቶ ከማመስገኑና ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ከመስጠቱ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንጀራን(ኅብስትን) በመቁረስ፣ ወይን የተሞላውን ጽዋ በማንሣት፣ የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት የምልክትነቱንና የምሥጢሩን ምንነት አስረዳ፤ ቀጥሎም የአደራረጉን ሥርዓት በመደንገግ ቅዱስ ቁርባንን መሠረተ (ማቴ 26፡ 26-30፤ ማር 14፡ 22-26፤ ሉቃ 22፡ 15-20)፡፡
ቅዱስ ቁርባን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያውና ደም አልባ መሥዋዕት ሆኖ ራሱን ለእያንዳንዱ ምእመን የሚሰጥበት ትልቅ ምሥጢር ነው፡፡
ቅዱስ ቁርባን የፍቅር ምልክት ነው፤
ቅዱስ ቁርባን የፍቅር ምልክት የተባለበት ዋናው ምክንያት ኢየሱስ ለዓለም ሕዝብ ደሙን አፍስሶ ፍቅሩን የገለጸበት ስለሆነ ነው፤ በተጨማሪም ምሥጢራዊ በሆነ መልኩ በሕዝቡ መካከል ስለሚኖርና የጌታችን መታሰቢያ የፍቅር ማዕድ ስለሆነ ነው(1ቆሮ 11፡ 26)፡፡ ቅዱስ ቁርባን ክርስቶስ በውስጣችን እንደሚያድር፣ ዘላለማዊ ሕይወት እንድናገኝ የሚያደርገንና መንፈሳዊ ረኃባችን የሚያስታግስልን የፍቅር ምሥጢር ነው(1ቆሮ 11፡ 33-34)፡፡
ቅዱስ ቁርባን የጌታ ሞትና ትንሣኤ የምናስብበት ምሥጢር ነው፤
ቅዱስ ቁርባን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቱንና ትንሣኤውን የምናስታውስበት፣ ክርስቶስ በልባችን ውስጥ እንደሚኖር የምናረጋግጥበት፣ ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር በሕይወት እንደምንኖር የምናረጋግጥበት ምሥጢር ነው፡፡ ኅብስቱን በምንበላበትና ጽዋውን በምንጠጣበት ጊዜ ሞቱንና ትንሣኤውን እናስባለን፤ እንመሰክራለን (1ቆሮ 11፡ 26)፡፡
ቅዱስ ቁርባን የአንድነት ምሥጢር ነው፤
ቅዱስ ቁርባን የአንድነት ምሥጢር የተባለበት ምክንያት ሁላችንም በአንድ ቤት ውስጥ ወደ መቅደሱ መጥተን ከአንድ ጽዋ በልተንና ጠጥተን ስለምንኖር ነው፡፡ የዘር፣ የፆታ፣ የቀለምና የወገን ልዩነት ሳይኖር ሁላችንም በአንድ መንፈስ፣ አንድ ዓላማ ይዘንና ተመሳሳይ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጅት አድርገን የምንቀበለው ምሥጢር ስለሆነ የአንድነት ምሥጢር ይባላል፡፡
ቅዱስ ቁርባን ከኃጢአት የማንጻት ኃይል ያለው ሕያው እንጀራ ነው፤
ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ሰዎች በተለይም አይሁዳውያን “ሕይወት የሚገኘው በደም ውስጥ ነው” የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ የሕዝቡን ኃጢአት ያስወግድ ዘንድ ደም ሁሉ በመሠዊያ ጐን እንዲፈስስ እግዚአብሔር ያዘዘበት ምክንያት የማንኛውም ሕያው ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ውስጥ ስለሆነ ነው (ዘሌ 17፡ 11፡ 14)፡፡ በዚህም መሠረት የክርስቶስ ደም ከኃጢአት የማንጻት ኃይል እንዳለው ይታወቃል፡፡
በቅዳሴ ሥርዓት ውስጥ በምሥጢራዊ መንገድ ተለውጦ የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን በእውነትም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡ ይህንን የምንቀበለውና የምናረጋግጠውም በእምነት ብቻ ነው፡፡ የክርስቶስ ደም የኃጢአት ይቅርታና ሰላምን ያስገኛል (ሮሜ 3፡ 25፤ ቆላ 1፡ 20)፡፡
ቅዱስ ቁርባን ኢየሱስ በአካል ባይኖርም ሕያው ሆኖ እርሱ በተወው የሕይወት እንጀራ አማካይነት በሕዝቡ መካከል እንደሚገኝ የምንረዳበት ምሥጢር ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን ኢየሱስ ሕይወት ሰጭ ሆኖ ራሱን ለሕዝብ የሚሰጥበት ምሥጢራዊ መንገድ ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን ኢየሱስ በሕዝብ መካከል እንዲሁም በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ውስጥ የሚኖርበት ምሥጢር ነው፡፡
ቅዱስ ቁርባን ሕይወት ሰጪ የሕይወት እንጀራ ነው፤
ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለ ሕይወት እንጀራ ከሌሎች ለየት ባለ መልኩ ገልጾታል፡፡ ኢየሱስ ከሰማይ የወረደው “ሕይወት ሰጪው የሕይወት እንጀራ” እንደሆነ እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡
የኢየሱስ ሥጋና ደም የማይጠፋና ዘላለማዊነት የተላበሰ የሕይወት ምግብ ነው(ዮሐ 6፡ 27)፡፡ የኢየሱስ ሥጋና ደም ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራና እውነተኛ መጠጥ ነው፤ ለዓለም ሕይወት የሚሰጥ ነው(ዮሐ 6፡ 32፡ 55)፡፡
የኢየሱስ ሥጋና ደም የሕይወት እንጀራ ነው፤ ይህንን የሚመገብ ከቶ አይራብም፤ አይጠማም (ዮሐ 6፡ 35)፡፡ የኢየሱስ ሥጋና ደም የሚቀበል ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ከቶ አይሞትም(ዮሐ 6፡ 51)፤ ሥጋውንና ደሙን የማይመገብ ግን ሕይወት የለውም(ዮሐ 6፡ 53)፡፡
የኢየሱስ ሥጋና ደም የሚቀበል ሁሉ በኢየሱስ ይኖራል፤ የሕይወት እንጀራ የሆነውን ሥጋና ደም በሚቀበሉት ሁሉ ላይ ኢየሱስ ሕያው ሆኖ ይኖራል (ዮሐ 6፡ 56)፡፡ የኢየሱስ ሥጋና ደም የሚቀበል የዘላለም ሕይወት አለው፤ ኢየሱስ በመጨረሻው ቀን ከሞት ያስነሣዋል(ዮሐ 6፡ 54)፡፡
ክርስቲያን የሆነ ሰው በመጀመሪያ ጽኑ የሆነ እምነት በኢየሱስ ላይ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የሚያምን ሰው የዘላለም ሕይወት አለው (ዮሐ 6፡ 47)፡፡ የሚያምን ሰው በእምነት አማካይነት ከኢየሱስ ጋር አንድ መሆን ይጀምራል፤ ኢየሱስን ይቀበላል፡፡
አብና ወልድ ሕያው ሆነው ለዘላለም እንደሚኖሩ ሁሉ ሕይወት ሰጭ የሆነውና ከሰማይ የወረደውን እንጀራ የሚመገቡት ሕያው ሆነው ይኖራሉ (ዮሐ 6፡ 57)፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድ ልጁን ሰጠ(ዮሐ 3፡ 16)፡፡ ይህ ወደ ዓለም የተላከው ልጁ ደግሞ ዓለምን እጅግ ስለወደደ ሕይወቱን ሰጠ፤ የእሱነቱ መገለጫ የሆነውን ሥጋውንና ደሙን ማለትም ቅዱስ ቁርባንን ሰጠ፡፡
ሰው ይህንን ሥጋና ደም ካልበላና ካልጠጣ ሕይወት እንደማይኖረው ኢየሱስ ይናገራል (ዮሐ 6፡ 53)፡፡ በእርግጥ እውነተኛ መብልና መጠጥ የሆነውን የኢየሱስ ሥጋና ደም የሚቀበል ሰው ኢየሱስ በውስጡ ያድራል፤ ይኖራል፤ ከኢየሱስ ጋር የአንድነት ጉዞ ያደርጋል(ዮሐ 6፡ 56)፡፡
ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነና የተላከ ነው (ዮሐ 6፡46) ፡፡ የተላከውም የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ለመፈጸም ነው(ዮሐ 6፡ 38)፡፡ የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ደግሞ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ነው(ዮሐ 6፡40)፡፡ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በኢየሱስ አምኖ ሕይወት ሰጭ የሆነውን ሥጋውንና ደሙን መቀበል ወሳኝ የሆነ የሕይወት ክፍል ነው፡፡
ቅዱስ ቁርባን የአዲስ ኪዳን መሥዋዕት ነው፤
መሥዋዕት አንድን ነገር በበጎ ፈቃድ ስለ ፍቅር ብሎ በታላቅ አክብሮት የሚሰጥ ወይም የሚሰዋ ገጸ በረከት ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፍቅርና በፍቅር ተሞልቶ ራሱን ለእኛ ለሰዎች ሕይወት እንዲሰጥ የተሰዋ መሥዋዕት ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን በየዕለቱ በመንበረ ታቦት የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት ነው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስና ቅዱስ ቁርባን
ከላይ እንደተገለጸው ሐዋርያው ጳውሎስ ቅዱስ ቁርባንን “የጌታ ራት” በማለት ይጠራዋል፡፡ የጌታ ራት የተመሠረተውም ጌታ ተላልፎ በተሰጠበት ሌሊት ነው (1ቆሮ 11፡ 23) ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብስቱን አንሥቶ የምሥጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ “እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ለእናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አላቸው(1ቆሮ 11፡24)፡፡
ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት መሠረተው (1ቆሮ 11፡25)፡፡ ስለዚህ ሥጋውና ደሙ እርሱን እንድናስብበት የተሰጠ ምሥጢር ነው፡፡
የጌታ ራት የሥጋ ረኃብ ማስታገሻ ሳይሆን ክርስቶስ በውስጣችን እንደሚያድር፣ ዘላለማዊ ሕይወት እንደምናገኝ የሚያደርገንና መንፈሳዊ ረኃባችን የሚያስታግስልን የፍቅር ምሥጢር ነው(1ቆሮ 11፡ 33-34)፡፡ የጌታ ራት በመሽቀዳደም የሚከናወን ሳይሆን በመከባበርና በፍቅር የሚከናወን ሥርዓት ነው(1ቆሮ 11፡ 33)፡፡
ማንም ሰው ይህን ኅብስት ከመብላቱና ይህንንም ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት ራሱን መመርመር አለበት (1ቆሮ 11፡ 28) ፡፡ ሰዎች ወደ ጌታ ማዕድ ከመቅረባቸው በፊት በመካከላቸው ልዩነት ካለ ማስወገድና ወደ አንድነት መንፈስ ማምራት ይኖርባቸዋል(1ቆሮ 11፡18)፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ቁርባን በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን፣ ሁላችንም እንደ አንድ ቤተሰብ የፍቅር ማዕድ የሆነውን በአንድነት ተካፍለን የአንድ አባት ልጆችና አንድ ቤተሰቦች መሆናችን የምናሳይበት ምሥጢር ነው፤ ማዕዱም ለዘላለማዊ ሕይወት የሚያዘጋጀን ነው፡፡
የመጀመሪያ ቁርባን ለመቀበል የደረሰ ልጅ ካለዎት፡ የልጆች እስተባባሪ የሆነውን አቶ መላከሰላም አየለን በስልክ ቁጥር 416-836 7435 ወይም በ ኢሜል አድራሻችን lmethiocatholic@gmail.com ይጠይቁ።
በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።