ምሥጢረ ጥምቀት

ምሥጢረ ጥምቀት

ምሥጢረ ጥምቀት

ጥምቀት በመጀመሪያው ከወላጆቻችን በአዳምና ሔዋን ምክንያት የወረስነውንና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን “የአዳም ኃጢአት” የሚያጠፋ፣ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበትን ጸጋ የሚያቀዳጅ፣ የክርስትና ጸጋ ተቀብለን የክርስቲያን ቤተሰብ አባል እንድንሆን የሚያበቃን ምሥጢር ነው፡፡

ጥምቀት በቅድስት ሥላሴ ስም የምንቀበለው ምሥጢር ሲሆን በውሃና በቅዱስ ቅባት አማካይነት ነጽተንና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ሆነን እንድንጓዝ የሚያደርገን ምሥጢር ነው፡፡ ጥምቀት ከኃጢአት ባርነት ነፃ ሆነን፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ በምናደርገው ጉዞ በር ከፋች ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ሚና የሚጫወት ምሥጢር ነው፡፡

ሰው በጥምቀት የቀድሞ ሕይወቱን ቀይሮ ወደ አዲስ ሕይወት ይገባል፤ በተመሳሳይ መልኩ ክርስቶስ በሞትና በመከራ አልፎ በትንሣኤው ክብር የተጐናጸፈው አዲስ ሰውነት ይለብሳል፡፡

 “ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” (ዮሐ 3፡ 5) ባለው መሠረት ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንድንችል ወሳኝ የሆነ ምሥጢር ነው፡፡

“ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ” የመታጠብና የመንጻት ሥርዓት መፈጸም ብቻ ሳይሆን ዋናውና ትልቁ ነገር የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መላበስ እንደሆነ ለማስገንዘብ ነው፡፡ በጥምቀት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንታተማለን፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንሆናለን፡፡

ነቢዩ ሕዝቅኤል ሕዝቡ በውሃ ተረጭተው ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር መንፈሱን እንደሚያሳድርባቸው ይናገራል (ሕዝ 36፡ 25-27)፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም እግዚአብሔር አስቀድሞ ውሃን እንደሚሰጥና ቀጥሎም መንፈሱን በሰዎች ላይ እንደሚያደርግ በመግለጽ ስለ ውሃና መንፈስ አስፈላጊነት ይናገራል፡፡

ውሃ ማጠብና ማንጻት የሚችል የንጽሕና ምልክት ነው፤ ሕይወትን የሚያረሰርስና የሚያረካ ምልክት ነው፤ በመሆኑም የእግዚአብሔር መንፈስ በውሃው አድሮ ኃጢአትን ያጥባል፤ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጠማቂውን ይሞላል፤ መለኮታዊ ጸጋ ተካፋይ በመሆን የእግዚአብሔር ልጅ እና የቤተ ክርስቲያን አባል ይሆናል፡፡  

ምሥጢረ ጥምቀት የተመሠረተው መቼ ነው?

የጥምቀት ምሥጢር የተመሠረተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፤ በጥምቀቱ ጊዜም መንፈስ ቅዱስ ወረደ፤ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚለው ድምፅ ከሰማይ ተሰማ፤ በዚህም የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር ተገለጠ (ማቴ 3፡ 13-17፤ ማር 1፡ 9-11፤ ሉቃ 3፡ 21-22)፡፡ 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቁ በተለያዩ ወንጌላውያን ተገልጿል፤ ነገር ግን እርሱ ሌሎችን ማጥመቁ አንድ ጊዜ ብቻ በዮሐንስ ወንጌል ተጠቅሶ እናገኘዋለን (ዮሐ 3፡ 22)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጥምቁ ዮሐንስ ይበልጥ ብዙ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርግና እንደሚያጠምቅ ፈሪሳውያን እንደሰሙ ቢገልጽም ወንጌላዊው ዮሐንስ ግን ያጠምቁ የነበሩት የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንጂ ኢየሱስ እንዳልነበር ይናገራል(ዮሐ 4፡ 1-2)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር “እኔ የምጠመቀው የመከራ ጥምቀት አለኝ፤ እርሱም እስኪፈጸም ድረስ ዕረፍት የለኝም” በማለት ስለሚጠመቀው የመከራ ጥምቀት ይናገራል (ማር 10፡ 38፤ 12፡ 50)፡፡ በእርግጥ የመከራ ጥምቀት በማለት የተናገረው ሞቱን ነው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ እና የጥምቀት ምሥጢር

እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አገላለጽ ጥምቀት በመጀመሪያ ከክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን ወይም ክርስቶስን በመምሰል የሚያስችለን ምሥጢር ነው (ሮሜ 6፡ 3)፡፡ ጥምቀት ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ በመለየት፣ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤን ምሥጢር ለመካፈልና በአዲስ ሕይወት መኖር የሚያስችለንን ጸጋ የሚያጐናጽፈን ምሥጢር ነው(ሮሜ 6፡ 3-4)፡፡

አንድ ሰው ሲጠመቅ ከክርስቶስ ጋር እንደተቀበረ ይቈጠራል፤ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሣ ሁሉ በጥምቀት ያለፈ ሰው ደግሞ ልክ ከሞት እንደመነሣት ያህል በክርስቶስ የትንሣኤ ምሥጢር ተካፋይ ይሆናል፡፡ በዚህም ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ ተለይቶ፣ የሞቱና የትንሣኤው ተካፋይነቱ ተረጋግጦ ከክርስቶስ ጋር አንድ የመሆኑንና ከእርሱም ጋር በሕይወት የመኖሩን ምሥጢር ያረጋግጣል (ሮሜ 6፡ 4-5፤ ቆላ 2፡ 12)፡፡

በጥምቀት የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ተካፋይ የሆነ ሰው በሞት የመለየት ያህል ከኃጢአት ተለይቶ፣ ክርስቶስ በሕይወቱ ነግሦ፣ የክርስቶስ ተባባሪ ሆኖ ይኖራል (ገላ 2፡ 20)፡፡

ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳችን የዘር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ እንዲሁም የሥልጣን ልዩነቶቻችን ትተን፣ ክርስቶስን ለብሰን በአንድ መንፈስ እንድንጓዝ የሚያደርገን ምሥጢር ነው(1ቆሮ 12፡ 13)፡፡

ሰዎች በውሃ ጥምቀት ይታጠባሉ፤ አዲስ ልደትም ይሆንላቸዋል፤ ቀጥሎም የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ሆነው ከክርስቶስና ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር አንድ ሆነው የመኖር ጸጋ ይቀዳጃሉ (1ቆሮ 12፡ 13፤ ቲቶ 3፡ 5)፡፡

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና ዮሐንስ በሐዋርያዊ ሥራቸው ውስጥ በጌታ ኢየሱስ ስም የተጠመቁ ሰዎች ሲያገኙ ይጸልዩላቸው ነበር፤ ቀጥሎም እጆቻቸው ይጭኑባቸውና መንፈስ ቅዱስ ይቀበሉ ነበር (ሐዋ 8፡ 15-17፤ 19፡ 5-6)፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መጀመሪያ መንፈስ ቅዱስ ተቀብለው በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጥምቀት የተቀበሉም አሉ (ሐዋ 10፡ 44-48)፡፡ ጌታ ኢየሱስ እኔና አብ አንድ ነን፤ እኔን ያየ አብን አይቶአል በማለት ተናግሮአል(ዮሐ 14፡ 9-14)፤ ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው መንፈስ ቅዱስ ቢቀበሉም ጥምቀቱ እግዚአብሔር አብንም ጭምር እንደሚወክል እንረዳለን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በተለምዶ የተለያየ የጥምቀት ዓይነቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

1.   የውሃ ጥምቀት

 ከላይ እንደተገለጸው የውሃ ጥምቀት ማለት አንድ ሰው በቅድስት ሥላሴ ስም በውሃ ተጠምቆ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ማደሪያ ሆኖ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ የመጠራት መብት አግኝቶና የቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆንበት መንገድ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ እንዳለበት ስለተነገረው በውሃ ይጠመቃል (ዮሐ 3፡ 5-6)፤ የቅድስና ሕይወት ጉዞ ይጀምራል፡፡

2.   የደም ጥምቀት

አንድ ሰው በውሃ ጥምቀት አማካይነት ከአዳምና ከሔዋን ኃጢአት ነፃ ወጥቶ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ለመኖር እየተዘጋጀ ሳለ ድንገት ሕይወቱ በሰማዕትነት (ስለ እምነቱ ሲመሰክር) ቢያልፍ በደም እንደተጠመቀ ይቈጠራል፤ ምክንያቱም በሞቱ ምስክርነት ሰጥቶአል፤ ደሙን ስለ እምነቱ አፍስሶአል፤ ስለዚህ የደም ጥምቀት እንደተጠመቀ ይቈጠራል፡፡

3.   የምኞት ጥምቀት

አንድ ሰው በምሥጢረ ጥምቀት አስፈላጊነት አምኖ፣ ለመጠመቅና የእግዚአብሔር ልጅ ለመባል ወስኖ በሚገኝበት ሰዓት ድንገት በሕመም ወይም በአደጋ ምክንያት ሕይወቱ ቢያልፍ በምኞት እንደተጠመቀ ይቈጠራል፡፡ የልብን ሁሉ መርምሮ የሚያየው እግዚአብሔር የዚህን ሰው እምነት አይቶ በዘላለማዊው ቤቱ እንደሚቀበለው ተስፋ በማድረግ የምኞት ጥምቀት ተቀብሎ እንዳለፈ ይታመናል፡፡

በጥምቀት ሥርዓት ላይ የምንጠቀምባቸው ምልክቶች እንዴት እንረዳቸዋለን?

  1. ውሃ

በተጠማቂው ራስ ላይ በመንከር የሚደረገው የውሃ ጥምቀት ተጠማቂው ከአዳም ከወረሰው ኃጢአት መታጠቡንና መንጻቱን፣ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገሩንና በአዲስ ልደት መወለዱን የሚያሳይ ነው፡፡ በእርግጥ ውሃ የሕይወት ምልክት እንደሆነ ይታወቃል፤ በመሆኑም አሮጌው ሕይወት መሞቱን፣ ከክርስቶስ ጋር መቀበሩን፣ ተጠማቂው በድጋሚ ሕይወት ማግኘቱንና መወለዱን የሚያሳይ ነው፡፡

2.   ቅዱስ ቅባት

ቅዱስ ቅባት የፈውስ፣ የኃይልና ብርታት ምልክት ነው፡፡ በድሮ ጊዜ ነገሥታት በቅዱስ ዘይት ይቀቡ ነበር፤ ይህም የተመረጡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናቸውን ለማሳየት ነበር፡፡ በተጠማቂው ግንባርና ጀርባ የሚደረገው ቅዱስ ቅባት ተጠማቂው ከእግዚአብሔር  ልዩ ጸጋ እንደሚሰጠው፣ የእግዚአብሔር ጥበቃና ከለላ እንደሚበዛለትና የእግዚአብሔር መልእክተኛ በመሆን እንደ ወታደር ሳይፈራ ስለ እምነቱ የሚመሰክርበት ኃይል ከእግዚአብሔር እንደሚሰጠው የሚያሳይና የሚያስገነዝብ ምልክት ነው፡፡

ቅዱስ ቅባት የጥምቀትን ጸጋ የሚያጠናክር እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም እኛም በክርስቶስ የንጉሥነት ክብር እንደተቀዳጀን የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡ ኢየሱስ መሲሕ ወይም የተቀባ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ እኛም በቅዱስ ቅባቱ ክርስቶሳውያን እንሆናለን፡፡ በመሆኑም የእግዚአብሔር መንግሥት የመስበክ፣ የማስተማር፣ የመምራትና የመፈወስ ኃላፊነት እንዳለብን የምንረዳበት መንገድ ነው፡፡

3.   ነጭ ልብስ

ከክርስቶስ ጋር ከሞት የመነሣት ምልክት ነው፡፡ በጥንት ጊዜ ክርስቲያኖች ልክ ከጥምቀተ ባሕር እንደወጡ ነጭ ልብስ ይለብሱ ነበር፤ ከክርስቶስ ጋር ሞተን ተነሥተናል ይሉ ነበር፡፡ ዛሬም ነጭ ልብስ በተጠማቂው ላይ የሚደረገው “ክርስቶስን ለብሰሃል”፤ “ክርስቶስ በሕይወትህ አድሮአል”፤ ለማለት ነው፡፡ መንጻቱን፣ ክርስቶስ መልበሱንና ከክርስቶስ ጋር ተሳስሮ አዲስ ሕይወት መኖር እንዳለበት የሚያስገነዝበው ነው፡፡

4.     የሻማ ብርሃን

ክርስቶስ በትንሣኤው የዓለም ብርሃን መሆኑን ታውቆአል፤ የትንሣኤው ብርሃን በዓለም ሁሉ ተዳርሶአል፡፡ በጥምቀት ጊዜ የሚለኰሰው ሻማ ደግሞ “የትንሣኤው ብርሃን በርቶልሃል፤ አንተም ለዓለም ብርሃን ሁን፤ በዓለም ውስጥ የክርስቶስ ትንሣኤ ብርሃን የበለጠ እንዲቀጣጠል አድርግ” ለማለት ነው፡፡

5.   የክርስትና አባት እና እናት

በጥምቀት አማካይነት ሕፃኑ በአዲስ መልክ ተወልዶአል፤ የክርስትና ሕይወትን አግኝቶአል፡፡ ስለዚህ ኃላፊነት ወስደው በእምነቱ የሚንከባከቡትና መልካም አብነት በመሆን የሚያስተምሩት በእምነታቸው ጠንካራ የሆኑ ክርስቲያኖች ያስፈልጋሉ፡፡ እነርሱ ባለ ዐደራ በመሆን እምነቱን በተግባር እንዲኖር ይከታተሉታል፤ የሥጋ ወላጆቹ ቢያጣ ደግሞ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉለት ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡ ከተጠመቀበት ሰዓት ጀምሮ እንደ ልጃቸው የመከታተል፣ የመምከርና በጥሩ ሥነ ምግባር የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ማጥመቅ የሚችለው ማን ነው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት “ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፤ በአብና በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጉአቸው” በማለት ላካቸው (ማቴ 28፡ 19)፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ማጥመቅ የሚችሉ የዛሬዎቹ ሐዋርያት በግልጽ ለይታለች፡፡

በመሆኑም የጥምቀት ሥርዓት በዋናነት የሚፈጽሙት ጳጳሳት፣ ካህናትና ዲያቆናት ናቸው፡፡ ቀጥሎም በተለያየ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ልዩ ፈቃድ የተሰጠው አንድ ካቲኪስት ማጥመቅ ይችላል፡፡ በመጨረሻም አንድ ሰው ሳይጠመቅ በሞት አደጋ ላይ ቢሆን ደግሞ ማንኛውም ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ ስም ሊያጠምቀው ይችላል፡፡ ተጠማቂው ሰው ከሞት አደጋ ከዳነ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ከካህናት ጋር በመነጋገር ተገቢውን ሥርዓት ማሟላት ይኖርበታል፡፡

ሕፃናት ገና በጨቅላ ዕድሜአቸው ለምን ይጠመቃሉ?

ጥምቀት በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኝ ሰው የቅድስት ሥላሴ ቤተሰብ እንዲሆን አስፈላጊ ምሥጢር ነው፡፡ በመሆኑም ሕፃናት ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የእግዚአብሔር ጸጋ ተላብሰው እንዲኖሩ መጠመቅ አለባቸው፡፡ ቤተሰብ ውስጥ ሕፃናት አሉ፤ ሕፃናት የቤተሰብ ክፍል ስለሆኑ በወላጆቻቸው እገዛ በጥምቀት ምሥጢር አማካይነት ከአዳም ኃጢአት ተፈትተው፣ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደው ያድጋሉ፡፡

ሊድያ የጌታ ቃል ሰምታ ካመነች በኋላ እርስዋና ቤተሰብዋ ሁሉ ተጠመቁ (ሐዋ 16፡ 15)፤ እስጢፋኖስና ቤተሰቡ በሙሉ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካይነት ተጠመቁ(1ቆሮ 1፡ 16)፡፡ በመሆኑም ሕፃናት ይጠመቃሉ፤ ከማንኛውም የሞት ሥጋትና የጨለማ ሕይወት ነፃ ሆነው ያድጋሉ፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ “በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆናችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል” ይላል (ገላ 3፡ 27)፤ በመሆኑም ሕፃናት ገና በለጋ ዕድሜአቸው ክርስቶስን ለብሰው እንዲያድጉ በወላጆቻቸው አማካይነት ይጠመቃሉ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሕፃናትን ተዉአቸው፤ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሉአቸው” ብሎ እጆቹን በመጫን ባረካቸው (ማቴ 19፡ 14)፡፡ ስለዚህ ሕፃናት ወደ ጥምቀት ምሥጢር ይመጣሉ፤ የጥምቀቱ ጸጋ ተካፋይዮች ይሆናሉ፤ በክርስትና መንፈስ እየዳበሩ ያድጋሉ፡፡

አንድ ሕፃን በስንተኛው መጠመቅ ያለበት መቼ ነው?

በመሠረቱ ሕፃን ለማስጠመቅ የጊዜ ገደብ ወይም የቀን ቆጠራ አያስፈልገውም፡፡ ከተወለደ በኋላ በየትኛውም ቀን ማስጠመቅ ይቻላል፤ ከተወለደ በኋላ ቶሎ እንዲጠመቅም ይመከራል፡፡ አንዳንድ አገራት በቀድሞ ዘመን ሕፃን ልጅ በተወለደ በሦስተኛው ቀን ያስጠምቁ ነበር፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በተወለደበት ቀን የሚያስጠምቁም ነበሩ፡፡

በአንዳንድ የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ በተለይም በምሥራቃውያን ዘንድ በተለምዶ ወንድ ልጅ በተወለደ በአርባኛው ቀን፤ ሴት ልጅ ደግሞ በሰማናኛው ቀን የማስጠመቅ ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ የቀን ውሳኔ የአዲስ ኪዳን መሠረት የለውም፡፡

በብሉይ ኪዳን ግን አንዲት እናት ሴት ልጅ ብትወልድ እስከ ሰማንያ ቀናት ድረስ፤ ወንድ ልጅ ብትወልድ ግን እስከ አርባ ቀናት ድረስ ወደ ተቀደሰው ድንኳን አትግባ፤ የተቀደሰም ነገር አትንካ፤ በእነዚህ ቀናት የመንጻት ሥርዓት ከፈጸመች በኋላ ወደ አምልኮ ድንኳን መግባት እንደምትችል የሚገልጽ ትእዛዝ አለ(ዘሌ 12)፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሁላችንም (ወንድም ሆነ ሴት) በክርስቶስ ደም ተረጭተን ድነናል፤ ርኩሰታችንና እርግማናችን ተወግዶልናል፤ ከብሉይ ኪዳን ሕግ ተፈትተናል፡፡ ስለዚህ የብሉይ ዘመን ወግና ሥርዓት በእኛ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሰዎች ላይ ተጽእኖ ሊፈጥር አይችልም፡፡

 

ልጅዎን ስለማስጠመቅ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በስልክ ቁጥር 647 995-8606  ወይም በ ኢሜል አድራሻችን lmethiocatholic@gmail.com ይጠይቁን።


በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።