አባ ቢንያም ያዕቆብ ከበደ
አባ ቢንያም ያዕቆብ ከበደ በ1974 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። የክህነት ጥሪ በተሰማቸው ጊዜ አዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ፍሪምናጦስ ንዑስ ዘርዓ ክህነት ገብተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኃላ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እዛው አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው በ (Capuchin Franciscan Institute of Philosophy and Theology) የፍልስፍና እና የሥነ- መለኮት ትምህርታቸውን ለሰባት ዓመታት ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላ ግንቦት 16 ቀን 2001 ዓ.ም በአዲስ ሀገረ ስብከት በልደታ ማርያም ካቴድራል በብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ እጅ ማዕረገ ክህነት ተቀብለዋል።
ክህነት ከተቀበሉም በኋላ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረዘይት ቅድስት ሥላሴ ቁምስና ፣ በቅዱስ ገብርኤል ቁምስና እንዲሁም በባሕርዳር ደሴ ሐዋርያዊ አስተዳደር በደብረ ማርቆስ ቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና በቆሞስነት እንዲሁም በሐዋርያዊ ጽ/ቤቱ በአስተባባሪነትና በሌሎችም ሃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል።
በ2012 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ጣልያን አገር ተልከው በቫቲካን ሀገር ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሌጅ (Potificio Collegio Etiopico) በመኖር በሮማ ከተማ በሚገኘው (pontifical university of St. Thomas Aquinas: Angelicum) በ “Spirutality” የድህረ ምረቃ ጥናታቸውን አጠናቀዋል።
ከሰኔ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በቶሮንቶ ልደታ ማርያም ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን አባ ኢሳይያስ ዱላን ተክተው መሪ ካህን እና በቶሮንቶ ሀገረ ስብከት የሆስፒታል Chaplain ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
አባ ኢሳይያስ ዱላ አርጋው
አባ ኢሳይያስ ዱላ አርጋው በ1962 ዓ.ም. ሰባት ቤት ጉራጌ በሚገኘው እምድብር ከተማ ውስጥ ተወለዱ። የከፍተኛ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው በ (Capuchin Franciscan Institute of Philosophy and Theology) በፍልስፍና እና በሥነ-መለኮት ለሰባት ዓመታት ተከታትለው አጠናቀዋል።
በ1990 ዓ.ም. የክህነት ማዕረግ ተቀብለው ለሚቀጥሉት 7 ዓመታት በወሊሶና በደብረዘይት ከተማዎች የቤተክርስትያን ቆሞስ በመሆን አገለገሉ። በተጨማሪም ለሁለት ዓመታት በካቶሊክ ወጣት ሰራተኖች ብሔራዊ እንቅስቃሴ መሪ ካህን ሆነው አገልግለዋል።
በ1997 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ጣልያን አገር ተልከው ሮማ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው ( Pontificia Universitas Lateranensis) በ“Social Doctrines of the Church” የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል።
ከ2002 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2015 ድረስ በቶሮንቶ ልደታ ማርያም ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን መሪ ካህን እና በቶሮንቶ ሀገረ ስብከት የሆስፒታል Chaplain ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አባ ኢሳይያስ ዱላ ከሰኔ 2015 ጀምሮ ሜፕል ከተማ በሚገኘው St David Parish ውስጥ ምክትል ቆሞስ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።