ምሥጢረ ክህነት

ምሥጢረ ክህነት

ክህነት የአገልግሎት ጥሪ ነው፡፡ ምሥጢረ ክህነት ማለት እግዚአብሔር ለአገልግሎት ከሕዝቡ መካከል የመረጠውን ሰው በመንፈሳዊነት፣ በዕውቀትና በሰብአዊነት በሚገባ ከታነጸና ከተዘጋጀ በኋላ የሚሰጠው የአገልግሎት ማዕረግ ነው፡፡

ምሥጢረ ክህነት የክርስቶስ የሊቀ ካህን አገልግሎት ሕይወት ተሳታፊና ተካፋይ የሚኮንበት ክቡር ምሥጢር ነው፡፡ የክህነት ምሥጢር የክርስቶስ የክህነት አገልግሎት የሚቀጥልበት መንገድ ነው፡፡ ከክርስቶስ የክህነት አገልግሎት መካከል የእረኝነት፣ የማስተማር፣ የማስተዳደር፣ ሕዝቡን ወደ ቅድስና የመምራትና የማስታረቅ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ምሥጢረ ክህነት በጳጳስ አማካይነት በዲቁና ማዕረግ ለሚገኝ ለአንድ አገልጋይ ሕዝቡን የበለጠ እንዲያገለግል የሚሰጥና የአገልግሎት ደረጃውን ከፍ የሚያደርግ ምሥጢር ነው፡፡ ጳጳሱም ከጸሎት ጋር በቅዱስ ቅባት ይቀቡታል፤ ለአገልግሎት እንዲሠማራም ያደርጉታል፡፡

እግዚአብሔር ከሕዝቡ መካከል የመረጠውንና ለአገልግሎት የጠራውን ሰው በተለያየ መልኩ በሰዎች አማካይነት በዕውቀት፣ በመንፈሳዊነትና በሰብአዊነት በበቂ ሁኔታ ታንጾ ከተዘጋጀ በኋላ ለአገልግሎት ይቀባል፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ማደሪያ ሆኖ በእረኝነት ሥራ ይሠማራል፡፡ 

አንድ ሰው ሲጠመቅ የንጉሥነት፣ የነቢይነትና የክህነት ማዕረግና ጸጋ ይቀዳጃል፤ ይህም የጋራ ክህነት ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሰው ለበለጠ አገልግሎት ለመሠማራትና ሕይወቱን ሙሉ የእግዚአብሔር ሆኖ ለመኖር በማሰብ ራሱን ሙሉ በሙሉ ይሰጣል፤ የክህነት ምሥጢር ይቀበላል፡፡

ምሥጢረ ክህነት ራስን ሙሉ በሙሉ በመካድ፣ በንጽሕና እየኖሩ፣ ባልተከፋፈለ ልብ እግዚአብሔርን ለማገልገል ለተዘጋጁት የሚሰጥ የአገልግሎት ማዕረግና ሕይወት ነው፡፡ ምሥጢረ ክህነት ሕዝብን ለማስተማር፣ መሥዋዕተ ቅዳሴ ለመቀደስ፣ ምሥጢራትን ለማደል፣ ቤተ ክርስቲያንን ያለማቋረጥ ለማነጽ፣ ሕዝብን ለመምራትና ለመቀደስ የሚሰጥ የአገልግሎት ምሥጢር ነው፡፡

የክህነት ምሥጢር አባትና እናት፣ ወንድምና እኅት፣ ልጆችም ሆነ ሌላ ንብረት ሁሉ ትቶ አገልግሎትን ብቻ መምረጥን ይጠይቃል (ማቴ 19፡ 29)፤ ስለ መንግሥተ ሰማያት ተብሎ ራስን እንደ ስልብ አድርጎ መቁጠርን ይጠይቃል(ማቴ 19፡ 12)፡፡

ምሥጢረ ክህነት ራሳቸውን ለአገልግሎት ላዘጋጁና በዚህ ሕይወት ለመኖር ቆራጥ አቋም ለሚያሳዩ ዲያቆናት በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ የአገልግሎት ምሥጢር ነው፡፡   

የክህነት ምሥጢር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱ እንዴት ይገለጻል?

የክህነት አገልግሎት መሠረቱ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ነው፡፡ የክህነት አመሠራረት በሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተለያየ መልኩ ተገልጾ ይገኛል፡፡ በእርግጥ የብሉይ እና የአዲስ ኪዳን ክህነት ተመሳሳይነትና ልዩነት አላቸው፡፡

ብሉይ ኪዳን 

እግዚአብሔር አስቀድሞ ለእስራኤላውያን “ለእኔም የተለያችሁ ቅዱሳን ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ እንደ ካህናትም ሆናችሁ ታገለግሉኛላችሁ” በማለት በክህነት ሕይወት ስለሚሰጠው የአገልግሎት ሕይወት ተናግሮ ነበር (ዘጸ 19፡ 6)፡፡

ቀጥሎም እግዚአብሔር አሮንንና ልጆቹን ካህናት ሆነው ያገለግሉት ዘንድ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል የተለዩ እንዲሆኑ አደረገ (ዘጸ 28-29፤ ዘሌ 8)፡፡ የሚያገለግሉትም እግዚአብሔርና ሕዝቡን ነው፡፡ አሮን ለክህነት አገልግሎት ከተመረጠ በኋላ የክህነት ልብስ እንዲለብስ ተደረገ፤ በቅዱስ ቅባትም ራሱን ቀቡት፤ “ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ” የሚል ቃል የተቀረጸበትን ጌጥ ሠርተው በራሱ መጠምጠምያ ላይ አኖሩለት(ዘጸ 29፡ 4-7)፤ እግዚአብሔርም ክህነቱን ባረከው(ዘሌ 21፡ 15)፡፡

ስለዚህ በመጀመሪያ የክህነት አገልግሎት እና ካህናት እንዲኖሩ የፈለገው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ የሚያገለግሉትም ሕዝቡን ነው፤ ዋና አገልግሎታቸው የራሳቸውንና የሕዝቡን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ማቅረብ ነው፡፡

ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ክህነት ምሥጢር ትልቅነት ሲናገር “በሰማይ ለመላእክት ያልተሰጠው ምሥጢር በምድር ለሰዎች ተሰጠ” ይላል፡፡ የካህናት ባልደረባ የሆነው ዮሐንስ ማሪያ ቪያኔ ደግሞ “ካህን ሌላው ክርስቶስ ነው” የሚለው መሠረት በማድረግ “ካህን በምድር ላይ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ጸጋ ተላብሶ የሚኖር አገልጋይ ነው” ይላል፡፡

የብሉይ ኪዳን ካህን አገልግሎት ምን ነበር?

የካህን ዋና የአገልግሎትና ተግባሩ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን ሕገ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ማስተማር ነው (ዘሌ 10፡ 11፤ ዘዳ 17፡ 18)፡፡ በሙሴ ሕግ መሠረት በሥርዓት ንጹሕ የሆነውንና ርኩስ የሆነውን ነገር ለይተው እንዲያውቁና እንዲያሳውቁ ነው(ዘሌ 10፡ 10፤ 2ነገ 12፡ 17)፡፡

ሌላው አገልግሎቱ በመቅደሱ ውስጥ ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን መባ እንዲያቀርቡና የተለያዩ የአገልግሎት ተግባራትን እንዲያከናውኑ ነው (ዘሌ 21፡ 8፤ ዘኁ 3፡ 7፤ 1ሳሙ 1፡ 3)፡፡ የራሱንና የሕዝቡን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርብ ነው(ዘኁ 18)፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲጠይቅ ነው(1ሳሙ 14፡ 36)፡፡ ካህን ለአገልግሎት የተለየ ስለሆነ ቅዱስ ሆኖ እንዲኖርና የእግዚአብሔርን ስም እንዲያከብር ተነግሮታል(ዘሌ 21፡ 8)፡፡

በአጠቃላይ ካህን እና ሊቀ ካህናት መሠረቱ ብሉይ ኪዳን ሲሆን ዋና ዓላማውም ለማስተማር፣ በመቅደሱ ውስጥ ለማገልገል፣ የራሱንና የሕዝቡን መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ለመጠየቅ፣ ለመዘመርና ለማሸብሸብ እንዲሁም የተለያየ አገልግሎት ለማከናወን የሚሰጥ የአገልግሎት ኃላፊነት ነው (2ዜና መዋ 5፡ 12-14፤ 31፡ 2፤ ኢሳ 61፡ 6፤ ሕዝ 40፡ 45፤ 44፡ 15)፡፡

በአንጻሩ ደግሞ አገልግሎታቸውን በሚገባ የማይወጡ ካህናት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸዋል፤ እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸውም ተነግሮአቸዋል (ሚል 1፡ 6-14፤ 2፡ 1-9)፡፡

አዲስ ኪዳን

የአዲስ ኪዳን ካህን ማን ነው?

እግዚአብሔር በመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ሊቀ ካህናት አድርጎ የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው (ዕብ 5፡ 10)፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ቅዱስ የሆነ፣ ያለ ነቀፋ የሆነ፣ ንጹሕ የሆነ፣ ከኃጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ ከፍ ያለ ነው(ዕብ 7፡ 26)፡፡

እርሱ ካህን የሆነው በሥጋዊ ሕግ መሠረት ሳይሆን በማይሻር ሕይወት ኃይል ነው፡፡ ምክንያቱም “እንደ መልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል (ዕብ 7፡ 17)፡፡

የአዲስ ኪዳን ክህነት (የክርስቶስ ክህነት) ተካፋይ የሚሆኑት እነማን ናቸው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጴጥሮስ አማካይነት ለሐዋርያት “በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል” በማለት የአገልግሎት ሥልጣን ሰጣቸው (ማቴ 16፡ 19)፡፡ ይህ የአገልግሎት ሥልጣን በክህነት ማዕረግ ለማገልገል ራሳቸውን የሚሰጡ ሁሉ የሚጋሩት ነው፡፡

ኢየሱስ የምስጋና ጸሎት አቅርቦ “እንካችሁ፣ ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያ አድርጉት፤” “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው” በማለት ሰጣቸው (ሉቃ 22፡ 17-20)፡፡ በዚህ ዓይነት ሐዋርያት ሥጋውንና ደሙን የመፈተት የአገልግሎት ኃላፊነት ተቀብለዋል፤ በተመሳሳይ መልኩ ዛሬ የክህነትን ምሥጢር ተቀብለው የሚያገለግሉ ሁሉ የዚህ የአገልግሎት ምሥጢር ተካፋዮች ይሆናሉ፡፡

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “አብ እኔን እንደላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ፤ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ግን ይቅር አይባልላቸውም” ብሎ መንፈሱን በላያቸው ላይ አፈሰሰ (ዮሐ 20፡ 20-21)፡፡ በክህነት አገልግሎት ለመሠማራት ራሳቸውን የሚያዘጋጁ ይህንን የአገልግሎት መንፈስ ይቀበላሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሞላሉ፤ ተልእኮውን ተቀብለው ወደ ሕዝቡ ሁሉ ይሄዳሉ፡፡

የክህነት አገልግሎት ምሥጢር የሚሰጠው እጅ በመጫን ነው፡፡ በዚህም የተለያዩ የአገልግሎት ስጦታዎች እንቀበላለን (2ጢሞ 1፡ 6)፡፡ ይህን የአገልግሎት ማዕረግ የሚሰጠውም ክቡር ሥራ ለማከናወን ነው(1ጢሞ 3፡ 1)፤ ክቡር ሥራውም ማስተማር፣ መስበክ፣ መቀደስ፣ መምራትና ምሥጢራትን ማደል ነው፡፡

በአገልግሎት ሕይወት ውስጥ ጳጳሳት፣ ካህናትና ዲያቆናት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተው፣ በቅዱስ ቅባት ተቀብተውና ልዩ ጸጋ ተቀዳጅተው ለአገልግሎት ይሠማራሉ፤ የክርስቶስ የአገልግሎት ክህነት ተካፋዮች ይሆናሉ፤ በእርግጥ የአገልግሎት ደረጃቸው በተወሰነ መልኩ ይለያያል፤ ነገር ግን ዋናው መሠረታዊ አሳቡና ዓላማው ትጉህ ሐዋርያ


 በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።