ምሥጢረ ሜሮን

ምሥጢረ ሜሮን

ምሥጢረ ሜሮን በጥምቀት የተቀበልነውን ጸጋ የሚያዳብርና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የምንሞላበት ምሥጢር ነው፡፡ ምሥጢረ ሜሮን ስለ እምነታችን ምንም ሳንፈራ “የእምነት ወታደሮች” ሆነን እንድንመሰክርና በእምነታችን ጽኑ እንድንሆን ኃይል የምናገኝበት ነው፡፡ ምሥጢረ ሜሮን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደታተምን የምናረጋግጥበት ምሥጢር ነው፡፡ 

በምሥጢረ ሜሮን ሙሉ በሙሉ የክርስቶስ ሆነን፣ በጸጋው ማኅተም ታትመን እንኖራለን፤ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ልጅ እንደሆነ ሁሉ እኛም በጸጋው ስለታተምን የክርስቶስ ወገኖች መሆናችን በምሥጢረ ሜሮን ይረጋገጣል፡፡

እግዚአብሔርን እንደ አባታችን “አባባ” ብለን መጥራት እንድንችል የልጅነት መንፈስ የምንለብስበት፣ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በልባችን ውስጥ እንዲያድርና እንዲታተም የሚያደርገን ምሥጢር ነው፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ተላብሰን፣ በዕውቀትና በጥበብ ተሞልተን፣ በእምነት፣ በፍቅርና በተሰፋ ለምልመን እንድንኖር የሚረዳን ምሥጢር ነው፡፡

   ሜሮን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን በሕይወታችን ውስጥ እንድንቀዳጅ የሚያደርገን ምሥጢር ነው(ኢሳ 11፡ 2፤ 1ቆሮ 12፡ 4-11)፡፡ ምሥጢረ ሜሮን ከክርስቶስና ከቤተ ክርስቲያን ጋር የበለጠ ተሳስረን እንድንኖር የሚያደርገን ምሥጢር ነው፡፡ በመሆኑም እምነታችንን እየኖርን፣ በቃልና በተግባር እንድንመሰክር የሚያደርገን ምሥጢር ነው፡፡ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከተሞሉ በኋላ በዓለም ሁሉ በድፍረት መመስከር ጀመሩ(ሐዋ 2)፤ በሰማዕትነም አለፉ፡፡

በሐዋርያት ዘመን ምእመናን ከተጠመቁ በኋላ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድባቸው ደቀ መዛሙርት እጆቻቸውን ጭነው ይጸልዩላቸው ነበር(ሐዋ 8፡ 14-18፤ 19፡ 1-6)፡፡ በተጠመቀ ክርስቲያን ላይ እጅ በመጫን መጸለይና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንዲሆን በር መክፈቱ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ የመጣ ሥርዓት ነው፡፡

የላቲን ሥርዓት በምትከተለው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከጥምቀት በኋላ ምሥጢረ ሜሮን በሀገረስብከቱ ጳጳስ አማካይነት ይሰጣል፡፡ በምሥራቃዊት ቤተ ክርስቲያን ግን በአብዛኛው ቦታ ተጠማቂው ሕፃን ሲጠመቅ ሦስቱንም ምሥጢራት ማለትም ጥምቀት፣ ሜሮንና ቁርባን አንድ ላይ ይቀበላል፤ እዚህም ቢሆን ሕፃኑ የሚቀባው ቅዱስ ቅባት(ሜሮን) ቀድሞውኑ በጳጳስ የተባረከ ነው፡፡

ምሥጢረ ሜሮን ልክ እንደ ምሥጢረ ጥምቀት ለአንድ ጊዜ ብቻ የምንቀበለው ምሥጢር ነው፡፡ በጥምቀት የተቀበልነውን ጸጋ የሚያዳብርና የክርስትና ጉዞአችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተሞላ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡

ምሥጢር ሜሮን እንደ ላቲን ሥርዓት ከጥምቀት በኋላ ዘግይቶ የሚሰጥ ከሆነ ለምሥጢረ ሜሮን የሚዘጋጀው ሰው ስለ “የእምነት ዐምዶች” በደንብ ማወቅና መረዳት አለበት፡፡ “የእምነት ዐምዶች” ከሚባሉት ውስጥ ዐሠርቱ ትእዛዛት፣ ሰባቱ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት፣ የቤተ ክርስቲያን ትእዛዛትና ጸሎተ ሃይማኖት የሚሉት ይገኙበታል፡፡             

 


በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።