የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት

የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት

ምሥጢር ማለት ምን ማለት ነው?

ምሥጢር ማለት ቀድሞ ተሸፍኖ የነበረ፤ አሁን ግን የተገለጠና የታወቀ እንደማለት ነው፡፡ ምሥጢር ቀድሞ በትንቢት ተነግሮ በድንግዝግዝ ሲታይ የነበረ፤ አሁን ግን ሁሉም ሊያውቀውና ሊረዳው በሚችል መልኩ የተገለጠና ይፋ የሆነ እውነታ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ቀድሞ በኦሪት፣ በነገሥታትና በነቢያት ዘመን ተሸፍኖ የነበረ፤ አሁን ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት የተገለጠና የታወቀ የእውነት ቃል ማለት ነው (ሮሜ 16፡ 25) ፡፡

ምሥጢራት ምንድን ናቸው?

ምሥጢራት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረቱና ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡ የጸጋ ምንጮች ናቸው፡፡ ምሥጢራት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤው ዓለምን አድኖ ከመሄዱ በፊት የመሠረታቸው የውስጣዊ ጸጋ ውጫዊ ምልክቶች ናቸው፡፡

ምሥጢራት በሰዎች ዐይን ለማይታየው ጸጋና በረከት ምልክት ይሆኑ ዘንድ በሚታይ መልኩ የቀረቡ የጸጋ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በሚታዩ ተጨባጭ ነገሮች አማካይነት የማይታየውን የእግዚአብሔር ጸጋ የሚተላለፍባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ምሥጢራት የሚታዩ ምልክቶች ሆነው በዐይን የማይታየውን የእግዚአብሔር ጸጋ ምንጮች ናቸው፡፡

ቁጥራቸው ሰባት የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት አሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሰባት ቁጥር ፍጽምና ወይም ሙልአትን ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ሰባቱ ምሥጢራት ሙሉ የሆነ መለኮታዊ ስጦታ ሲሆኑ የጸጋ ሀብት በሙልአት የምናገኝባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ 

ምሥጢራት የጸጋ ምንጭ ሆነው እንዲያገለግሉ፣ የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያንጹና ወደ ቅድስና ሕይወት በሚደረገው ጉዞ እንዲረዱ የተሰጡ ግልጽና ተጨባጭ ምልክቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሕፃን የቅዱስ ቅባት ዘይት በጥምቀትም ሆነ በሜሮን ጊዜ ይቀባል፤ ቅዱስ ቅባቱ በዐይን የሚታይ ተጨባጭ ምልክት ነው፤ ነገር ግን ቅዱስ ቅባቱ በዐይን የማይታየውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ጸጋ ለመቀበል ምልክት ሆኖ ያገለግላል፡፡   

ምሥጢራት መለኮታዊውን ጸጋ በሕይወታችን ውስጥ እንዲያድርና መንፈሳችን እንዲለመልም ይረዱን ዘንድ የተሰጡን የፍቅር ምልክቶች ናቸው፡፡ ምሥጢራት የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ጸጋ አግኝተን፣ ከብዙዎች ጋር በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሆነን እንድንኖርና ዕለታዊው ሕይወታችን አጠናክረን እንድንቀጥል የሚረዱን ስጦታዎች ናቸው፡፡

ምሥጢራት ክርስቲያኖች በቅድስና መንገድ እንዲጓዙ የሚረዱ፣ የሚያንጹ፣ የሚያስተምሩ፣ እምነትን የሚያጠናክሩና የሚገልጹ መንፈሳዊ ሀብታት ናቸው፡፡ ምሥጢራት ከቅድስት ሥላሴ ጋር ተዋውቀንና ተሳስረን እንድንኖር የሚረዱን የጸጋ ሀብታት ናቸው፡፡ ምሥጢራት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት፣ ንጉሥነትና ነቢይነት የምንካፈልበት ጸጋን የሚያቀዳጁን ናቸው፡፡

ምሥጢራት በኃጢአታችን ተጸጽተንና ንስሓ ገብተን፣ ከእግዚአብሔር፣ ከኅሊናችን፣ ከወንድም እኅቶቻችንና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ታርቀን በቅድስና እንድንኖር የሚረዱን ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ ሕመምና ሥቃይ በበዛ ጊዜ በቅዱስ ዘይት አማካይነት ኃይል አግኝተንና ተዘጋጅተን ወደ ዘላለማዊ ቤታችን እንድንጓዝ የሚረዱን ናቸው፡፡

በአጠቃላይምሥጢራትበዐይንየማይታየውንቀዳሽጸጋየምናገኝባቸውግልጽምልክቶችናቸው፡፡በምሥጢራትአማካይነትየጸጋሙልአትለማግኘትየእያንዳንዱሰውመንፈሳዊዝግጁነትወሳኝነትአለው፡፡አንድሰውበቂናአስፈላጊውንመንፈሳዊዝግጅትአድርጎምሥጢራትሲቀበልበጸጋላይጸጋይቀዳጃል፡፡

ሰባቱ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት በሦስት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም፦

1. የመጀመሪያዎቹ ምሥጢራት፦ የመጀመሪያዎቹ ምሥጢራት የሚባሉት ጥምቀት፣ ሜሮን እና ቅዱስ ቁርባን ናቸው፡፡ እነዚህ ምሥጢራት ከቤተ ክርስቲያንና ከክርስቶስ ጋር እንድንተዋወቅና የቤተ ክርስቲያንና የክርስቶስ አካል ክፍሎች እንድንሆን የሚረዱን ናቸው።

          2. የምሕረትና የዕርቅ ምሥጢራት፦ የምሕረትና የዕርቅ ምሥጢራት የሚባሉት ንስሓ እና ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው፡፡ እነዚህ ምሥጢራት ከእግዚአብሔር ጋር እንድንታረቅና ምሕረት እንድናገኝ የሚረዱን ናቸው፡፡

          3. የአገልግሎት ምሥጢራት፦ የአገልግሎት ምሥጢራት የሚባሉት ምሥጢረ ክህነትና ተክሊል ናቸው፡፡ እነዚህ ምሥጢራት የሕይወታችን መንገድ ለይተን፣ ቃል ኪዳን ገብተን በተለያየ መልኩ እግዚአብሔርና ሕዝብን እንድናገለግል የሚያደርጉን ምሥጢራት ናቸው።


በአባ ምስራቅ ጥዩ (ዶ/ር) ከተዘጋጀውየእምነት በር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።