ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብለው መሰየማቸውን ቫቲካን ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. አወጀ።

ክቡር አባ አባ ተስፋዬ ታደሰ ዘማኅበረ ኮምቦኒ በመስከረም 12, 1962 ዓ.ም. ( 22/09/1969 እ.ኤ.አ.) በሐረር ከተማ የተወለዱ ሲሆን ከተወለዱ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ቤተሰባቸው የመኖሪያ ከተማ ወደ አዲስ አበባ መጡ።በአዲስ አበባ ከ 1ኛ እስከ 8ኛ በሰፈራቸው በነበሩት ትምህርት ቤቶች በምስራቅና በነጻነት ብርሃን ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሲሆን፣ ከ9ኛ ክፍል እሰከ 12ኛ በቦሌ አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።በአዲስ አበባ የመድኃኔ ዓለም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወጣት ማኅበር አባል እያሉ፣ አስራ ሁለተኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ፣ በ1979 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባለው የኮምቦኒ ዘርዓ ክህነት ገቡ። በካፑቺን ፍራንሲስካውያን የፍልስፍናና የነገረ መለኰት ተቋም የፍልስፍና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከዚያም በአዋሳ ከተማ በማኅበረ ኮምቦኒ ተመክሮ አድርገው በሚያዝያ 23: 1983 ዓ.ም ከሌሎች ወንድሞች ጋር የመጀመሪያ መሃላቸውን አደረጉ።ከዚያም ወደ ሮም ከተማ ለነገረ መለኮት ትምህርት ተልከው በግርጐርያን ዮኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ከዚያም በዛው በሮም ባለ የቤተክርስቲያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሰለ ሌላ እምነቶች በተለይ ሰለ እስልምና ሃይማኖት የድህረ ምረቃ ተጨማሪ ትምህርታቸውን የጀመሩ ሲሆን በሮም ከተማ በጥቅምት 22/1987 ዓ.ም የመጨረሻ መሃላቸውን አድርገዋል። በታህሳስ 28/1987 በሮም ከረዳት ጳጳስ ክሌመንቴ ሪቫ እጅ ማዕረገ ድቁናን ተቀብለዋል።

ከዚያም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ከብፁዕ አባታችን ካርዲናል ጳውሎስ ጻድዋ እጅ ማዕረግ ክህነትን በቁምስናቸው በመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በነሐሴ 20/1987 ተቀብለዋል። ከሲመተ ክህነታቸው በኋላ ወደ ካይሮ ከዚያም ወደ ሮም ተልከው የጀመሩትን ትምህርትን ቀጥለዋል። ከዚያም ወደ ሱዳን ተመድበው በካርቱም ከ 1990-1993 ዓ.ም. በሐዋርያዊ ስራ አገልግለዋል። ከዚያም ወደ ሮም ተመልሰው የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ከዚያም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለሁለት ዓመት ያህል በአዋሳ ሀገረ ስብከት ባሉ ሁለት ቁምስናዎች በሃሮ ዋቶ ጕጂና በቱሎ ሲዳማ የሐዋርያዊ ስራና የትምህርት ቤት አገልግሎት ሰጥተዋል።ከዚያም ወደ ሮም ተልከው በሳሌዝያውያን ዮኒቨርሲቲ ሰለዘርዓ ክህነት የሕንፀት አገልግሎት አጭር ኮርስ አድርገው ጉለሌ ባለው የማኅበረ ኮምቦኒ ዘርዓ ክህነት አገልግሎት ሰጥተዋል። በተጓዳኝ በጉለሌ ፍራንሲስካውያን የፍልስፍና የነገረ መለኰት ተቋም አስተምረዋል።

ከ 1994-1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የማኅበረ ኮምቦኒ አለቃ አማካሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ይሄንም አገልግሎት እየሰጡ ሳሉ በ1998 ዓ.ም በኢትዮጵያ የማኅበረ ኮምቦኒ አለቃ ሆነው እንዲያገለግሉ የተመረጡ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት አገልግሎት በኋላ እንደገና ተመርጠው ሁለተኛ ዙር እያገለገሉ ሳሉ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ የካቶሊክ ገዳመዊ ማኅበራት አለቆች ጉባዔ ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል። አገልግሎታቸውን መስጠት እየቀጠሉ በሮም በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ በጥቅምት 2002 የኮምቦኒ ማኅበር ጠቅላይ አለቃ አማካሪ ሆነው ተመረጡ። በመስከረም 2008 ዓ.ም በሮም በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ የኮምቦኒ ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ሆነው ተመረጡ። በሰኔ 2014 እንደገና ጠቅላይ አለቃ ሆነው ተመረጡ። በሮም የማኅበራትና የገዳማት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ለሶስት ዓመት ያገለገሉ ሲሆን በሕብረቱ ስም በተለያዪ አገልግሎቶች የተሳተፉ ሲሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት ስለሲኖዳዊ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የሲኖዶስ ልዑክ ሆነው ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ደስታውን እየገለጸ ለክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰ የተባረከ የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸው ይመኛል፡፡

Next
Next

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2016 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት