በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የልደታ ማርያም ቤተሰቦች - እንኳን ለ2016 ዓ.ም. የሆሳዕና በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። ይህ ታላቅ በዓል ቤተክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት ስታከብረው የቆየ- በክርስትና እምነት ውስጥም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው …

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የልደታ ማርያም ቤተሰቦች - እንኳን ለ2016 ዓ.ም. የሆሳዕና በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ።

ይህ ታላቅ በዓል ቤተክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት ስታከብረው የቆየ- በክርስትና እምነት ውስጥም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው - እንዲሁም በክርስትና እምነት ውስጥ - ትልቅ አሻራ የሚያሳርፍ በዓል ነው። ይህ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ - የደህንነት ምስጢር ለመፈጸም - ወደ ፍጻሜ የሚገባበትና - ምድራዊ ተልዕኮውን ለማጠናቀቅ - ወደ እየሩሳሌም የሚያቀናበት ታላቅ ዕለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መልኩ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ - በእርግጥም ለምን ዓላማ እንደሚገባና - በዛም የሚያጋጥመውን ሁሉ በሚገባ ያውቃል - ይህንንም የማቴዎስ ወንጌል 20፥17 ጀምሮ በዝርዝር ያስቀምጣል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም መንገድ ከመጀመራቸው በፊት - 12ቱን ሐዋርያቶች ለብቻቸው ጠርቶ - እንግዲህ አሁን ወደ እየሩሳሌም እንወጣለን - የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፊዎች ተላልፎ ይሰጣል-  እነሱም የሞት ፍርድ የፈርዱበታል - አሳልፈውም ለአሕዛብ እንዲዘባበቱበት - እንዲገርፉትና - እንዲያሰቃዩት - በስተመጨረሻም እንዲሰቅሉት አሳልፈው ይሰጡታል - ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ግን- በ3ኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ - የጨለማውንም ሃይል ሁሉ ረግጦ ይነሳል ብሎ ነግሮአቸዋል።

ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም በሚሄድበት ጊዜ - ዓላማና ግቡን በልቡ ይዞ - ሰለሚመጣው መከራና ስቃይ አምኖበት - የመጣበትን የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም - ወደ ታላቋ ከተማ ወደ እየሩሳሌም - ወንድሞቹን አስከትሎ ተጓዘ። በ1ኛ ቆሮንጦስ 15፥ 36 በተጻፈው መሰረት - ማንኛውም የሚዘራ ፍሬ ካልሞተ ፍሬ እንደማያፈራ - ካልሞተ ሕይወት እንደማይኖረው በመገንዘብና - የእርሱ ሞት ለአሕዛብ ሁሉ - የዘለዓለማዊ ሕይወት ምንጭ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት - የእርሱ ሞት ለአሕዛብ ሁሉ ዘለዓለማዊ ደህንነት የሚያመጣ መሆኑን ስለሚያውቅ - ሕይወቱን ስለ በጎቹ ሲል ለመስጠት - የመጨረሻውን ሰዓት ምድራዊ ጉዞውን ጀመረ ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ - ይህ በአህያይቱ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም የመግባቱ ትንቢት - አስቀድሞ በትንቢተ ዘካርያስ 9፥9 ላይ የተተነበየ - መፈጸምም የሚገባው የቡልይ ኪዳን ትንቢት ሲሆን - ቃሉም እንዲህ ይላል።  አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ - አንቺ የእየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ - እነሆ ንጉስሽ ጻድቅና አዳኝ ነው - ትሁትም ሆኖ - በአህያይቱም ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ - ወደ አንቺ ይመጣል ይላል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም ንጉሥ ሆኖ ሲገባ-  ንግሥናው ዓለማዊ ባለመሆኑ - በሰንጋ ፈረስ ወይም በሰረገላ ላይ ሆኖ ሳይሆን - የትህትና እና የልፋት ምሳሌ በሆነችው - በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ነበር።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም የሚገባበትን - ማንም ሰው ያልተቀመጠባትን ውርንጭላ እንዲያመጡለት - ከደቀመዛምርቱ ሁለቱን ልኳቸው እንደነበር - የማቴ. ወንጌል 21፥2 ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን። ሁላችንም እንደምናውቀው - በቡሉይ ኪዳን ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ሁሉ - በኩር የሆነና- ከእህልም ከሆነ - የመጀመሪያው  ፍሬ መሆን እንዳለበት - በኦሪት ዘሌዋውያን እንዲሁም በሌሎቹም የኦሪት መጻሕፍት ላይ ተዘርዝሮ አናገኘዋለን። በተመሳሳይ መንገድ - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን ራሱን መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ - ወደ መስዋዕቱ ቦታ እየተጓዘ በመሆኑ - ማንም ሰው ያልተቀመጠባት ውርንጭላ ማስፈለጉ ሰለዚህ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የበኩር ልጅ ነው - ከዛም በላይ ራሱ ፍጹም አምላክ ነው - ስለዚህ ይህ የበኩር እና ፍጹም የሆነው አምላክ - ራሱን ለሰው ልጆች ደህንነት - ለመስዋዕትነት ለማቅረብ ሲጓዝ - ይህን የተቀደሰ መስዋዕት ይዞ የሚጓዘው እንስሳም - ንጹህ መሆን ስለነበረበት - ይቺ ማንም የልተቀመጠባት ውርንጭላ አስፈለገች። ይህ ሁሉ የሚያመላክተን - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቡልይ ኪዳን - ስለእርሱ የተጻፉትን ትንቢቶች ሁሉ - አንድም ሳያስቀር በምድራዊ ሕይወቱ ተግብሯቸዋል - ለዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቡልይ ኪዳን ፍጻሜ በእርሱ ተከናወነ - እርሱ የቡልይ ኪዳን መደምደሚያ - የአዲስ ኪዳን ደግሞ መክፈቻ ቁልፍ ነው ብለን የምንመሰክረው።

ደቀመዛምርቱ የአህያዋን ውርንጭላ ካመጡለት በኋላ-  ልብሳቸውን በአህያዋ ውርንጭላ ላይ አነጠፉ- ይህም ለእርሱ ታዛዢ መሆናቸውንና - እርሱንም እንደ ንጉስ መቀበላቸውን የሚያመሳክር ነበር። ኢየሱስም በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ - ወደ እየሩሳሌም በታላቅ እልልታና ደስታ ሲገባ - ብዙ ሰዎች ደስታቸውን ለመግለጽ - አንዳንዶቹ ልብሳቸውን በመንገዱ ላይ በማንጠፍ - ሌሎቹ ደግሞ የደስታና የድል ምልክት የሆነውን - የዘንባባ ዝንጣፊ በመሬቱ ላይ ይጎዘጉዙ ነበር። እንዲሁም በዛ የተገኙትም ሁሉ - ሆሳዕና በአርያም - በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው - ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ - ሆሳዕና ለኢየሱስ - ሆሳዕና ለክርስቶስ በማለት - በታልቅ ድምጽ ይጮሁ ነበር።

ሆሳዕና ማለት የእብራይስጥ ቃል ሲሆን - ቀጥተኛ ትርጉሙ - መዳን ወይም አዳኝ በሚለው ሊተረጎም ይችላል። በዛን ጊዜ በዙሪያው የነበሩት ሰዎች - ይህ ሁሉ ደስታቸውና እልልታቸው - ምን አልባት እነሱ ይጠብቁት የነበረው ነቢይ - ከሮማውያኑ አገዛዝ ነጻ የሚያወጣቸው ነቢይ - እንደ ሳኦልና ዳዊት - እንደ ንጉስ ሰሎሞን - እስራኤላውያኑን በዙሪያቸው ካሉ ጠላቶቻቸውና - ጫና ከሚያሳድሩባቸው የአካባቢው ገዢዎች - ነጻ የሚያወጣ -የሚያድናቸው ነቢይ አድርገው ስለውትም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በእርግጥም እነሱ ሙሉ በሙሉ አይረዱት እንጂ - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ መግባቱ - የሰውን ልጅ ሁል ጊዜም ከሚያስጨንቀውና - ጨቁኖ ከያዘው - የእግዚአብሔር ልጅነትን ጸጋ ከሚያሳጣው  ኃጢአትና - ከዲያቢሎስ እስር  ነጻ ሊያወጣው  - ከዘለዓለማዊ ሞት ሊያድነው የመጣ ነቢይ ነው። ይህንንም በትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 61 - ላይ ለድሆች የምስራችን እሰብክ ዘንድ - ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ - ለተማረኩትም ነጻነትን - ለታሰሩትም መፈታትን  አውጅ ዘንድ - የሚያለቅሱትንም እንዳጽናና - በለቅሶም ፈንታ የደስታን ዘይት -  በኃዘን መንፈስም  የመጽናናት መጎናጸፊያን እንደሰጥ ልኮኛል በሚለው ቃሉ ይገልጸዋል።

በሉቃስ ወንጌል 21፥39 ላይ - ከፈሪሳውያኑ ወገንና መምህር የነበሩት - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማሳደድና ለማስወገድ ያሴሩ የነበሩት - ደቀመዛምርቱን - እንዲሁም በእልልታና በሆታ ያጀቡትን ሕዝቡን ሁሉ - ዝም እንዲያሰኝ እንደነገሩት ይነግረናል - ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ - እነሱ ዝም ቢሉ እንኳን - ድንጋዮች ይጮሃሉ ብሎ መልሶላቸዋል። ይህም የሚያሳየን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስበኃይሉና በስልጣኑ - አውሎ ነፋስን ጸጥ የሚያሰኝ - ታላላቅ የባሕር ወጀቦችን የሚገስጽ - ሽባውን የሚተረትር - የጎበጠውን የሚያቀና - የጠፋውን ዓይን የሚያበራ - ለሞተዉም መልሶ ነፍስን የሚዘራ - በቃሉ ብቻ ዓለማትን የፈጠረ - ዓለምና በእርሷ ውስጥ ያሉት ሁሉ የሚታዘዙለት - አቻ የሌለው አምላክ መሆኑን ነው።

የዛሬው የዕብራውያን መልዕክት - ከምዕራፍ 9 ላይ ያነበብነው - በብሉይ ኪዳን ዘመን ይካሄድ እንደነበረው - ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት እንዲቀርቡ - ለኃጢአታቸው ካሣ የሚሆን - በካህኑ አማካኝነት ታርዶ የሚቃጠለው  ኮርማና ፍየል - የሚረጨውም የእንስሳቱ ደም  - ከእንግዲህ ወዲህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስደም እንደተተካ ይነግረናል።የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስመስዋዕት ፍጹም ነው - በመሆኑም እንደ እንስሳቱ ደም - በየጊዜው የሚታረድና የሚረጭ ሳይሆን - በመስዋዕቱ - ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ - የሰውን ልጅ ሁሉ - ዘለዓለማዊ ደህንነትን የሚያጎናጽፍ ነው።

ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቱ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም የሚጓዘው - የሁላችንን የኃጢአት እዳ ለመክፈል ነው - እኛን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ሊያወጣን ነው - ያውም ለአንድና ሁለት ጊዜ ሳይሆን - ለዘለዓለሙ ሊቤዤን ነው። በጀመሪያዎቹ በቡልይ ኪዳን ዘመናት - የእግዚአብሔር ማደሪያው - የቃል ኪዳኑ ድንኳን ነበር - ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መስዋዕት በደሙ ከከፈለልን በኋላ ግን - የእግዚአብሔር ማደሪያ - የቃል ኪዳኑ ድንኳን ሳይሆን - የእያንዳዳችን ሰውነት ነው። ይህንንም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ምዕራፍ 12፥1 ላይ ሲያረጋግጥልን እንዲህ ይለናል - ወንድሞችና እህቶች ሆይ - እንግዲህ ሰውነታችሁ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና - ሕያው - ቅዱስም መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ - በእግዚአብር ርህራሄ እለምናችኋለው ይለናል።

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም የታጠበው - የተቀደሰው ሰውነታችን - ዘለዓለማዊ ደህንነትን የተጎናጸፈው እኛነታችን - ይህን ቅድስናውንና - ንጽህናውን ይዞ መቀጠል የሚችለው  -ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይዞ መጓዝ እስከቻለ ጊዜ ብቻ ነው። ይህንንም አብሮነት ለማስቀጠል - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምስጢራት አማካኝነት መንገዱን አበጅቶታል - ስለዚህ ይበልጥ ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስየሚያቀራርበንን - ምስጢረ ንስሃና ምስጢረ ቁርባን - አዘውትረን በመቀበል - ይህንን ከእርሱ ጋር ያለንን አንድነታችንን እናጠናክር። ይህንን እውነታ ወንጌላዊው ዮሐንስ 15፥4 ጀምሮ እንዲህ ይገልጸዋል - በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ - ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር- በራሱ ምንም ዓይነት ፍሬ ማፍራት እንደማይችል ሁሉ - እናንተም በእኔ ባትኖሩ - ምንም ማድረግ አትችሉም - እኔ የወይን ግንድ ነኝ - እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ - ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና - በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ እኖራለሁ - ብዙ ፍሬም ያፈራል ይለናል። ስለዚህ የወይኑ ግንድ ከሆነው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ህብረታችን ካልጠነከረ - በህይወታችን ምንም ዓይነት መልካም ፍሬ ልናፈራ አንችልም።

ዛሬ በ2ኛ መልዕክት ከ1ኛ ጴጥ. 4 ላይ ያነበብነውም-  ከዚሁ ሃሳብ ጋር የሚስማማ መልዕክት ይነግረናል - እንዲህም ይለናል - እንግዲህ በስጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን - እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጅ - እንደ ሰው ምኞት አትኑሩ ይለናል። ሰው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖር - የረጋ አይምሮ ያስፈልገዋል - በተረጋጋ አእምሮ ከክርስቶስ ጋር ሕብረቱን ካቆመ - ባልእንጀራውን እንደ ራሱ መመልከት - ከእግዚአብሔር በተቀበለውም ጸጋና- ከእርሱ በሚመነጨው ኃይልና ብርታት - እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ መመላለስ - በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ቤት - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የከፈለለትን  ዘለዓለማዊ ሕይወት መቋደስ ያስችለዋል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንድንችል - ከልደቱ እስከ ትንሣዔው አብራው የተጓዘችው እናቱ እመቢታችን ቅድስት ድንግል ማርያም - ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ - ይህንን የሆሳዕና በዓል በረከትና ጸጋ ለእያንዳዳችን ታሰጠን - በዓላችንን የበረከትና ብዙ- መንፈሳዊ ጸጋ የምንሰብስብበትም ያድርግልን።

Next
Next

ዘመጻጒዕ የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት