የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እ.አ.አ. በ2020 ዓ.ም. ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ እና አንድ መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጋለች። በ2021 የአውሮፓውያን ዓመትም ከሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዛለች።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን የ2013 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ ጳጳሳት፣ የልማት ኮሚሽኑ የቦርድ አባላት እና የስበካ ጽ/ቤቶች ተወካዮች በተገኙበት ረቡዕ መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን በመላው ኢትዮጵያ በ13 ካቶሊካዊ ሰበካዎች ሃይማኖትን፣ ዘርን፣ ጾታን፣ የኑሮ ደረጃ ልዩነቶችን ወይንም ማናቸውንም በሰዎች መካከል ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ ምክንያቶችን መሰረት ሳያደርግ ለሰው ልጆች በሙሉ ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ዕድገትን የሚያመጡ የፍቅር ሥራ አገልግሎቶችን በማቅረብ ኢትዮጵያውያንን በእኩል የሚያገለግል የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት ነው። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በማሕበራዊ የልማት ኮሚሽን አማካኝነት ከምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች መካከል የጤና፣ የትምህርት፣ የምግብ ዋስትና፣ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎቶች ይገኙባቸዋል።
ኮሚሽኑ በ2013 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤው እ.አ.አ. 2020 ዓ.ም. አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አፈጻጸም እና የኦዲት ሪፖርቶችን በማድመጥ እንዲሁም የ2021 ዓ.ም. የሥራ ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ አጽድቋል። ቤተክርስቲያኒቱ በ2020 ዓ.ም. በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች አንድ መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ፕሮጀችቶችን ተግባራዊ አድርጋለች። በዚህም በመላው ኢትዮጵያ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ አድርጋለች። በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች በሕብረተሰቡ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ከተከሰቱት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች መካከል የኮቪድ 19 ወረሺኝ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የጎርፍ አደጋ እና በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ለበርካቶች ሞት፣ መፈናቀል እና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑት ጦርነት እና ግጭቶች ይገኙበታል። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለእነዚህ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት በሐዋርያዊ እና በልማት ኮሚሽኖቿ በኩል በቀጥታ ተግባራዊ ከምታደርጋቸው ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ አጋር ለጋሾችን በማስተባበር ከ40,000,000 (አርባ ሚሊዮን ብር) በላይ የሚገመት ገንዘብ በማሰባሰብ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ለጉዳት ለተጋለጡ ወገኖች ለምግብ፣ ምግብ ነክ ላልሆኑ ቁሳቁሶች፣ ለመድሃኒት፣ ለኮቪድ 19 ህክምና እና የመከላከያ ቁሳቁሶች ስርጭት ለተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ራሽን በማቅረብ አፋጣኝ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።
ከገንዘብ እና የዓይነት ድጋፎች በተጨማሪ ቤተክርስቲያኒቱ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ መስፋፋትን ለመግታት የሚያስችሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስመልክቶ መመሪያ በማውጣት በሁሉም የአምልኮ ስፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማቶቿ ተፈጻሚ እንዲሆኑ እያደረገች ትገኛለች።
በተጨማሪም ከ80,000,000.00 (ሰማንያ ሚሊዮን ብር) በላይ በማሰባሰብ በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በሌሎችም ክልሎች በጦርነት እና የተለያዩ ግጭቶች ለጉዳት ለተጋለጡ እና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የዓይነት፣ የገንዘብ እና የምግብ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።
በኢትዮጵያ በሚገኙ የካቶሊክ እርዳታ ድርጅቶች፣ ሀገረስብከቶች፣ ገዳማት እንዲሁም ተቋማት በኩል በአጠቃላይ ከ1,000,000,000 (አንድ ቢሊዮን ብር) በላይ የሚገመት ገንዘብ በድጋፍ ሥራ ላይ በማዋል በሀገራችን ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ ላይ ናት። በእነዚህ ተግባራትም ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ወገኖችን ተጠቃሚ አድርጋለች። በቤተክርስቲያኒቱ በማዕከል ከሚከናወኑ የድጋፍ ተግባራት በተጨማሪ እያንዳንዱ ሀገረስብከት በተለይ ደግሞ የጦርነት እና ግጭት ሰለባዎች የሆኑት የአዲግራት እና የባህር-ዳር ደሴ ሀገረስብከቶች በየበኩላቸው ሕዝባቸውን በማረጋጋት ለተጎጂዎች የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ጦርነት እና ግጭቶችን በተመለከተም ቤተክርስቲያኒቱ ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋርም ሆነ በግሏ ችግሮች ከመባባሳቸው በፊት በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በሙሉ ከግጭት አስተሳሰብ ወጥተው ወደ ጦርነት ሊያስገቡ የሚችሉ ሁኔታዎችን በአፋጣኝ በማቆም ልዩነቶቻቸውን በጠረቤዛ ዙሪያ በውይይት እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ይፋዊ ጥሪዎችን አስተላልፋለች። በሽምግልና ተግባራት በመሳተፍ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ የግጭት ውጥረቶች እንዲረግቡ ጥረት አድርጋለች። በየአካባቢው በሚከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶች ንጹሐን ዜጎችን ለሞት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት ውድመት የሚዳርጉ ተግባራት እንዲቆሙ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አስተላልፋለች። አሁንም የንጹሐን ደም እንዳይፈስ፣ ሕዝቦች እንዳይፈናቀሉ እና ሁሉም ለሰላም መስፈን ተባባሪ እንዲሆን በድጋሚ ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
በሀገር ውስጥ የሚገኙ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ገዳማትን፣ ምእመናን፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አስተዳደር እና ሠራተኞችን በማስተባበር ሀገራችንን በገጠማት ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ልዩ ጸሎቶች እና ምህለላዎች እንዲደረጉ ጥሪ በማስተላለፍ፣ ከበጎ አድራጊዎች የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በተለይም በትግራይ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ በጳጳሳት የሚመሩ የልዑካን ቡድኖችን በመላክ ጉብኝት በማድረግ በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመመልከት፣ የማጽናናት እና የአብሮነት መግለጫ ይፋዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ እንዲሁም ከሕዝብ በተሰበሰበ እገዛ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፎችን በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። በተጨማሪም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል ይቻል ዘንድ በ2021 የአውሮፓውያን ዓመት የልማት ኮሚሽኑ (ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር) በላይ በመመደብ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዟል።