ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የዘንድሮውን ዐቢይ ጾም በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የዘንድሮውን ዐቢይ ጾም በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ
“የተወደዳችሁ ካቶሊካውያን ምእመናን፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኙ ሁሉ፣ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሰዎች በሙሉ የእግዚአብሔር አምላክ ጸጋና ሰላም በያላችሁበት ይድረሳችሁ።
የዐብይ ጾም ወራት የክርስቶስን ስቃይ ሞትና ትንሳኤን ለማክበር የምንዘጋጅበት የሊጡርጊያ ወቅት ነው፡፡ በጾም ወራት ካቶሊካውያን ምእመናን ሶስት ነገሮችን በስፋት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይኸውም መጸለይ፣ መጾምና ምጽዋትን መስጠት ናቸው፡፡ እነዚህም የቤተክርስቲያን ትእዛዛት ናቸው።
ይህ የጾም ጊዜ ንስሐ በመግባት ከአምላክና ከሰው ጋር የምንታረቅበት ጊዜ፣ በጸሎት ፈጣሪን የምንለምንበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር የምንሆንበት ጊዜ፣ እንዲሁም ካለን ለሌላቸው የምናካፍልበት የምጽዋት ወቅት ነው። ስለ ምጽዋት ሲናገር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡ ‘ድሆች ከሃብታችን እንዳይካፈሉ መከልከል ከእነርሱ መስረቅ፣ ሕይወታቸውንም መንሳት ነው፡፡ የያዝነው ኃብት የእኛ አይደለም የእነርሱ እንጂ’ (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁጥር 2446)።
አርባ ቀናትና አርባ ሌሊት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያመለክተው የፈተና የንስሐ የመንጻትና የመታደስ ጊዜ እንደሆነ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ 40 ቀናት ኢየሱስ ወንጌልን የመስበክ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በበረሃ የተፈተነበትን ጊዜ ያመለክታል፤ ‘መንፈስ ቅዱስም …ወደ በረሐ መራው፤ በሰይጣንም እየተፈተነ አርባ ቀን በበረሐ ቆየ’ ይላል (ማር.1፡12-13)።
አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት የኑሮ መወደድና የሰላም መታጣት ፈተና ውስጥ መሆናችንን እንረዳለን። በመሆኑም በዚህ የጾም ወቅት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈተናዎች እንድናስብና መልክታቸው ምንድን ነው የሚለውን እንድናስተነትን ግድ ይለናል።
በጾም ወራት ከምንጋፈጣቸው ነገሮች አንዱ ከዓለምና ተሸክመነው ከምንዞረው ስጋችን እንዲሁም ከሰይጣን በኩል የሚመጡብን ፈተናዎች ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ የተፈተነባቸው ሶስት ፈተናዎች የእኛም ፈተናዎች ናቸውና እንዳይጥሉን እንዘጋጅ። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው።
ሥጋዊ ምቾትን የመሻት ፈተና
‘ፈታኙም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፥ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ’ አለው። ኢየሱስም፥ ‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል’ ሲል መለሰለት (ማቴ.4፡3-4)። ይህ ፈተና ስጋዊ ምቾትን የመሻት ፈተና ልንለው እንችላለን። ሆድ ሲሞላ የምግብ ጥያቄ ሲመለስ ስጋችን ሌላም ነገር ይሻል፣ ድሎትን፣ ስጋዊ አምሮት እንዲሟላለት ይፈልጋል፣ ይህም አንዱ ፈተናችን ነው። የምንደክመው ጠግበን ለመብላት ብቻ ሳይሆን አማርጠን ለመብላት ጭምር ነው።
ሰዎች ለመኖር መብላት አለባቸው፤ ለመብላት ደግሞ መስራት የግድ ነው። ቅዱስ ጳውሎስም ያለው የማይሰራ አይብላ የሚል ነው። ‘እንጀራዬ ለእኔ መስታወቴ ነሽ፣ ሁልጊዜ የሰው ፊት ታሳዪኛለሽ’ እንደሚለው የሰው ፊት የሚያሳየን የእንጀራ ጉዳይ ነው። ስራ ያለው ሰርቶ ሲበላ ስራ ያላገኘ ሰው ሲንከራተት ማየት ያሳምማል፤ የኑሮ ውድነት እንኳንስ የሚበላ ነገር ለማማረጥ ቀርቶ በቀን ሦስት ጊዜ ለመብላት የሚቸገሩ ቤተሰባቸውን የሚያቀምሱት አጥተው ጭንቅ የዋጣቸው ቤቱ ይቁጠረው፤ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት እድል የሚፈጠረው።
በርግጥ ደልቷቸው የሚኖሩ ነገር ግን ሰዎች ተርበዋል ቢሏቸው ረሃብ ምን እንደሆነ በእውነትም የማይገባቸው ጥቂት ሰዎች አይጠፉም። እኛ ግን ይህንን ጾም በምንጾምበት ጊዜ የተራቡ ወገኖቻችንን የምናስብበትና ካለን የምናካፍልበት ሊሆን ይገባል። ከምግብ መራቅ አንዱ የመጾሚያ መንገድ ሲሆን የተራቡትን መመገብና ካለን ለሌሎች ማካፈል ሁለተኛው ነው። ፈተናችን እዚህ ላይ ነው፣ ምን ያህል ተካፍለን እንበላለን? የምንኖረው ለመብላት ነው ወይስ ለመኖር ነው የምንበላው? ሰዎች ተርበዋል የሚበሉት ነገር የለም ስትባል ለምን ኬክ አይበሉም እንዳለችው ንግስት እኛ በልተን ስናድር ሁሉም ሰው በልቶ የሚያድር ይመስለን ይሆን? ራሳችንን ማየት መፈተን ይኖርብናል፣ ፈተናውን ልናልፍ ይገባል፣ ካለን ላይ በማካፈል ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር በማሳየት፣ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ሰፊ ቦታ በመስጠት፣ ስጋን በጾም ማስራብና እየተራበ የሚጾመውን ሕዝባችንን የመመገብ ኃላፊነትን ምን ያህል እንወጣለን የሚለውን ፈተናችንን የምንመልስበት መንገድ የሚታይበት ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ከዲያብሎስ የቀረበለት ፈተና ስልጣኑን በመጠቀም ድንጋዩን ወደ ዳቦ እንዲለውጥ የሚል ነበር። እኛም በተሰጠን ስልጣን ልንሠራ የሚገባን ለእግዚአብሔር ክብርና ለጋራ ጥቅም መሆኑን ያስታውሰናል። በዛሬ ጊዜ ራሳችንን መጠየቅ የሚገባን ስልጣናችንና ኃላፊነታችን ልምዳችንና ትምህርታችን ሳይማር ላስተማረንና እንድናገለግለው ለመረጠን ሕዝብ ጥቅም እያዋልነው ነውን ወይስ አይደለም የሚለው ነው፤ ፈተናችን ይህ ነው፣ ምን ያህል ለገባነው ቃል ኪዳን በመኖር ሕዝባችንን በቅንነትና በታማኝነት እናገለግላለን፣ በእውነት የሚያገለግሉትን ምን ያህል እናመሰግናለን፣ ተበለሻሸ ለምንለው አሰራር መስተካከል ምን ያህል እንጸልያለን፣ ከዚህም ባሻገር ኃላፊነታችንንና ስልጣናችንን በመጠቀም ለእግዚአብሔር ፈቃድ ምን ያህል እንገዛለን የሚል ሊሆን ይገባል።
ትኩረትን የመሻት ፈተና
በሁለተኛው ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ የተጠየቀውና ያለፈው ፈተና ትኩረትን የመሻት ፈተና ነው። ቀጥሎም ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ በመውሰድ ከቤተ መቅደሱም አናት ላይ አውጥቶ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ ‘እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል፣ በእጃቸው ያነሱህ ዘንድ፣መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል’። ኢየሱስም እንደዚሁ በመጻሕፍት፥ ‘እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ተጽፏል’ (ማቴ.4፡ 5-7) በማለት መለሰለት።
በእግዚአብሔር ላይ ከመተማመንና እሱን ከመታዘዝ ይልቅ ተአምር ካላደረክ ብሎ እሱን የማዘዝ ያህል ማስቸገር እርሱን መፈታተን ይሆናል። ለምሳሌ ሰላም እንደሚያስፈልገን እያወቅን የሰላም መሣሪያ ለመሆን ከሁሉም ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት ማድረግ ሲገባን እንዲያው በደፈናው ጌታ ሆይ የሰላም መሳሪያ አድርገኝ ማለት ብቻውን በቂ አይሆንም፣ ስለዚህ ፈተናችን የሚሆነው የሚጠበቅብንን እናደርጋለን ወይስ የእኛን ድርሻ ለፈጣሪ በመተው ተአምር እንዲያደርግ እንጠብቃለን።
በራሳችን ለራሳችን ማድረግ የሚገባንን ነገር ማድረግ እየቻልን እርሱ ካላደረገ ማለት አምላክን እንደመፈታተን ነው፤ ለምሳሌ የምንራመድበትን እግር እስከሰጠን ድረስ በእግራችን መራመድ ሲገባን ክንፍ ካልሰጠኸኝ ብሎ ተአምር መጠበቅ እርሱን መፈታተን ያስመስልብናል። በዚህ የጾም ወራት የምንፈተነው ተአምር ፈላጊዎች ነን ወይስ በእምነት አምላካችንን እንታዘዛለን፣ የምንፈልገውን ነገር ሠርተን ከማግኘት ይልቅ በአቋራጭ እንዲሆንልን ወይም ተአምር እንዲደረግ የምንሻ ከሆነ ፈተናውን ወድቀናልና እንደገና ቃሉን ታጥቀን ምላሽ በመስጠት ፈተናውን ልናልፍ ይገባል””
ይህ ፈተና አምላካችንን ጠይቀን እርሱ በእኛ በኩል በሚያከናውናቸው ነገሮች አማካይነት እኛ በሰዎች ዓይን እንድንደነቅ ትኩረትን የመፈለግ ፈተና ነው። መታየት፣ መሰማት፣ መወደድ፣ መደነቅ ወዘተ…ፈተናዎቻችን ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ከፍ ከፍ ሊል እኛ ግን ዝቅ ዝቅ ልንል እነዚህ የጾም ወራት ይጋብዙናል።
ምድራዊ ስልጣንን የመሻት ፈተና
ሦስተኛው ጌታችን ኢየሱስ የተፈተነው ጥያቄ እግዚአብሔርን በመካድ ምድራዊ ስልጣንን እንዲቆናጠጥ የተሰጠው ምርጫ ነው። እንደ ገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ አወጣው፤ የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየውና፣ ‘ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ’ አለው። ኢየሱስም፣ ‘አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏልና’ አለው (ማቴ.4፡9-10)።
ጌታችን ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ወንጌሉን ይሰብክ ዘንድ የአባቱን ተልእኮ ሊፈጽም ነፍሳትን ለማዳን የጠፉትን ለመፈለግ ተልእኮ ሲሆን ዲያብሎስ ያቀረበለት ጥያቄ ፈታኝነቱ አምላክን ከማገልገልና እርሱን ከማምለክ ይልቅ ለእኔ ተገዛ አገልጋይ ሁን የሚል አንድምታ ያለው ነው። የጌታችን ኢየሱስ መልስ ግን ከሰይጣን ጋር መስማማትን ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክን ማምለክ ለእርሱ ብቻ መስገድና ለእርሱ አገልጋይ መሆን እንደሚገባ አስረግጦ ይናገራል።
ዛሬም የብዙዎቻችን ፈተና እግዚአብሔር አምላክ በሰጠን ስልጣን ባስቀመጠን የኃላፊነት ቦታ ላይ በፍቅር እናገለግላለን? ሲሾም ያልሰራ ጡረታ ሲወጣ ይጸጸታል እንላለን ወይሰ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል በሚል ዓይነት ስልጣናችንን አላገባብ እየተጠቀምን ነው? ሌሎች በአገልግሎታችን ይደሰታሉ? አምላክን ያመሰግናሉ? ወይስ በእኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ይማረራሉ? ይህ የጾም ወቅት ራሳችንን የምናይበትና የምንፈተንበት ጊዜ ነው። ኃላፊነት ከሰሩበት ካገለገሉበት በረከቱ ለሁላችንም ነው፤ ፈተናችን የሚሆነው መስራት በሚገባን ጊዜና ቦታ ለሕዝባችን ማገልገል ሲገባን ስልጣናችንን ለማሳየትና ሌላ ተጨማሪ ከፍያ ተጨማሪ ክብር ከፈለግን፣ በማገልገላችን ልንከበር ሲገባ ቦታው ላይ በመቀመጣችን ብቻ ክብር ካልተሰጠን የሚል ስሜት ከተሰማን፣ ፈተናውን ወደቅን ማለት ነው። ፈተና የምንወስደው ለማለፍ እንጂ ለመውደቅ አይደለም፤ በዚህ የጾም ወራት ፈተናችንን ለማለፍ ልንዘጋጅ ይገባል። እንዲሁ የሚደረግ ጾም የለምና ለጥያቄአችን መልስ እንድናገኝና እግዚአብሔርን በማዳመጥ ፈቃዱን ለማድረግ እንጹም።
እግዚአብሔር አምላክ ፈተናችንን አልፈን፣ ንስሐ በመግባት ከእርሱና ከሰዎች ሁሉ ጋር ታርቀን ካለን ላይ ለወገኖቻችን አካፍለን እርሱ ወደፈለገው የፍቅርና የሰላም ኑሮ መኖር እንድንችል ጾምና ጸሎታችንን ይቀበልልን፡፡ ለትንሳኤው ብርሃን በሰላም ያድርሰን።
አገራችን ኢትዮጵያን ይባርክልን ! እርቀ ሰላሙን ያውርድልን ! አሜን!”