መዘምራን
“የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።”
—ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡16
“ለእግዚአብሔር አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፤ ምስጋናው በቅዱሳኑ ጉባኤ ነው። እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፥ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤትን ያድርጉ። ስሙን በዘፈን ያመስግኑ፥ በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት”
— መዝሙረ ዳዊት 149፡1-3
የዝማሬ ሚና በቤተክርስትያን ውስጥ
ከጥንት ጊዜ አንስቶ የቅዳሴ ስርዓተ ክብርን ከፍ ለማድረግ፣ ውበቱና ታላቅነቱን ለመግለጽ እንዲሁም የአገልጋይ
ካህናት መንፈሳዊ ልምድንም ለማሳደግ ሙዚቃና ዝማሬ አንዱ አስፈላጊ የክርስትና አካልና ልምድ በመሆን ቆይቷል፡፡
“ብሉይ ኪዳን በዳዊት መዝሙር ምዕራፍ 149 ቁጥር 1 እግዚአብሔርን አመስግኑ። ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር
ዘምሩ፤ መንፈሳውያን ሰዎች በጉባኤ አመስግኑት” ይላል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ሥርዓተ
አምልኮ አከባበርን በሚመለከት አንቀጽ 1156 ላይ እንዳሰፈረው “አብዛኛውን ጊዜ በሙዚቃ መሳሪያዎች የሚታጀቡ
መንፈሳዊ መዝሙራት ቅንብርና ዜማ ከብሉይ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮ አከባበሮች ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡ ቤተ
ክርስቲያን ይህንን ትቀጥልበታለች፤ ታስፋፋዋለችም“ በማለት ያሰምራል። አዲስ ኪዳን በቆላስይስ ምዕራፍ 3 ቁጥር
16 እንዲህ ያሳስባል። “የክርስቶስ ቃል በሙላት በእናንተ ይኑር፤ ከእናንተ አንዱ ሌላውን በጥበብ ሁሉ
ያስተምር፤ ይምከርም፤ በመዝሙርና በውዳሴ፤ በመንፈሳዊ ዜማም እግዚአብሔርን ከልብ እያመስግናችሁ ዘምሩ።“
ሙዚቃና ዜማ በማዕከላዊነት ስርዓተ ቅዳሴውን ከፍ እንደሚያደርጉ በመታመኑ ለዚህ ዓላማ የሚተጉ ዘማሪዎችና
የሚያቅፋቸውም ተቋም ተሰየመ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህ ተቋም በቤተክርስቲያን ውስጥ አስፈላጊ ተግባሮችን እንደ ሊቀ
ጳጳስ ሚናዎችን የሚፈጽሙ የአማኞችን ስብስብ ፈጠረ፡፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አንቀጽ
1156 በመቀጠል ሲያብራራ ”የኩላዊት ቤተክርስቲያን ዝማሬና ሙዚቃ ባህል ከግምት በላይ ዋጋ ያለው፣ ከማናቸውም
ዓይነት ሥነ ጥበብ እንኳ የላቀ ሀብት ነው፡፡” ስለሆነም ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እስከ ተሃድሶ ድረስ፣ የሙዚቃ
ታሪክ በመሠረቱ ከቤተ ክርስቲያን የሙዚቃ ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ነበር ፡፡ ”የዚህም ታላቅነት ዋናው ምክንያት፣
የተቀደሰ ሙዚቃና ቃላት ጥምረት እንደመሆኑ የሚመስጥ ሥርዓተ አምልኮ ሁነኛ አካል ይሆናልና ነው።”
የተቀደሰ ሙዚቃና ዝማሬ በቅዳሴ ሥርዓት ጊዜ ለተካፈሉ ሁሉ መንፈሳዊ ሙላትና ደስታ ይሰጣሉ፡፡ ይህንን ቅዱስ
አገልግሎት በተመለከተ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከቤተክርስቲያን ታላላቅ ቅድመ አባቶች ሊቃውንት አንዱ የሆነው
ቅዱስ አውገስጢኖስ፣ የተካነ የሥነ-መለኮት ምሁርና ታዋቂ፣ ሰባኪ፣ የጽሁፍ ባለሙያና የቤተክርስቲያን ዶክተር፣
ጸሎት ከዝማሬ ጋር ሲዋሃድ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን ያሰምር ነበር። “የሚዘምር ፣ ሁለት ጊዜ ይጸልያል”
ማለቱም ይታወሳል፡፡
ለኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የግዕዝ ቋንቋ ሥነ አምልኮ የተቀደሰ ሙዚቃና ዝማሬ ባህል ቅዱስ ያሬድ ትልቅ
አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የኖረው ኢትዮጵያዊው ሙዚቃ ደራሲ፣ የሙዚቃ
አቀናባሪ፣ ምሁር የሆነው ቅዱስ ያሬድ ትምህርቱ በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የግዕዝ ሥነ-ሥርዓታዊ
ዝማሬዎችን በአራት ዓመታዊ ክፍሎች ፣ ማለትም በልግ ክረምት፣ በጋ፣ መኸርና ፣ ፀደይ ወቅታትን የሚወክሉ የሙዚቃ
ዜማዎችን አቀናጅቷል፡፡ እርሱ ለሙዚቃ ፍቅር ስለነበረው የቅድስት ሥላሴ ምስጢርን የሚያንፀባርቅ የሙዚቃ
ምልክቶችን እንዲሁም በርካታ ሃይማኖታዊ የየራሳቸው ጣዕመ ዜማ ያላቸው መዝሙሮችን እና ዜማዎችን
ፅፏል፡፡ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ በመካከለኛው ዘመን ታላቅ የሙዚቃ ሥራ ፈጣሪ ነው ፡፡ የሙዚቃው ምልክቶች አሥር
ሲሆኑ እነርሱም ይዘት፣ ደረት፣ ርክርክ፣ ድፋት፣ ጭረት፣ ቅናት፣ ሂደት፣ ቁርጥ፣ ድርስና አንብር ይባላሉ፤
እያንዳንዳቸውም ልዩ ትርጉም አላቸው፡፡ እነዚህ የ ቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ፈጠራዎች ዛሬም የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን
የግዕዝ ቋንቋ ሥነ አምልኮ ውስጥ ላለው የተቀደሰ ሙዚቃና ዝማሬ መሠረት ናቸው፡፡
ስለሆነም የመዘምራን ዋና ሚና፣ በቅዳሴ ሥርዓት መዝሙር በመዘመር እግዚአብሔርን ማወደስና ማክበር፣ ከካህኑ ጋርም
በመንፈስ መገናኘት ነው ፡፡ ጥሩ የመዘምራን ተቋም ለመገንባት፣ ለመዘመር ፍቅርና ተሰጥኦ ያላቸው፣ ቢቻል ሙዚቃ
መሳሪያዎችን የመጫወት ችሎታ ያላቸው ትጉ አባላት ያስፈልጉታል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለልምምድና ለክብረ በዓላት
ጊዜ በተመደቡበት ቅዳሴ ሥርዓት ላይ ለመገኝት ሙሉ ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል።
የቤተክርስትያናችን መዘምራን ልምምዳቸውን የሚያደርጉት ዘወትር ማክሰኞ ከ 6፡00 pm እና እሁድ ከቅዳሴ በፊት 1፡30 pm ጀምሮ ነው። እርስዎም የመዘምራኑ አባል ሆነው መሳተፍ ከፈለጉ በቤትክርስትያኑ ኢሜይል አድራሻ lmethiocatholic@gmail.com ይጻፉልን።