ከአቅም በላይ የሆነውን ጉዳያችሁን ለርሱ ተውት

 

እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው። በተፈጠሩ ወይንም በፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ የበላይ ገዢ ነው። ይህንን እናውቃለን እናምናለንም።

በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ቁ 48 ላይ እንደተጻፈልን፣ ደቀመዛሙርቱ በባሕር ላይ ሆነው ሲጓዙ በነፋስ ማዕበል ምክንያት መቅዘፍ አቅቷቸው  በተጨነቁ ሰዓት ኢየሱስ ክርስቶስ በርጋታ ውኃው ላይ እየተራመደ ሄዶ እነርሱ በነበሩበት ጀልባ ላይ  ሲወጣ ማዕበሉ እንደቆመ ይነግረናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየተራመደ የመጣው እኛ ችግር ነው ልናልፈው አንችልም የምንለው እክል ላይ ነው፤ አስቸጋሪ ጉዳያችን ላይ ነው፤ ለእኛ ከአቅም በላይ ነው ባልነው ነገር ላይ ነው። ደቀመዛሙርቱ የተሰቃዩት በማዕበሉ የመጣ ነው፣ ክርስቶስ ደሞ በዚያው ችግር በሆነው ማዕበል ላይ ነው እየተራመደ የመጣው።

እስቲ ወደራሳችን ማዕበል መለስ ብለን እናስተውል።  ዛሬ እኔና እናንተ ፊት ያለው ማዕበል ምንድነው? ይህ የሕይወቴ ማዕበል ነው የምንለው ነገር አለ? የቤተሰብ ሃሳብ፤ የልጆች ጉዳይ? የጤና መታወክ፤ ኢኮኖሚ፤ ሥራ ማጣት፤ አለመመቻቸት፤ የትዳር ጉዳይ? አጠቃላይ የሕይወት ውጣ ውረድ የሆነብን ማዕበል፤ ፊታችን ያለው ጦርነት፤ ዘወትር የምንሰማው በሽታ፤ ወረርሽኝ፤ ረሃብ፤ ፈጣሪያችን ከነዚ ማዕበል በሙሉ በላይ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ በገላቲያ ለተሰደዱት ክርስቲያኖች 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፥7 ላይ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት ብሎ ነግሯቸዋል ።

ጭንቀት የሚፈጠረው ከአቅማችን በላይ ስናስብ ጭምር ነው፣ ከአቅም በላይ የሆነውን ጉዳያችሁን ለርሱ ተውት ይላል ቅዱስ ጴጥሮስ። የሚያስጨንቀን ከአቅማችን በላይ ከሆነ ማረፍ የምንችለው በእርሱ ላይ የመጣል ፍጹም እምነት ሲኖረን ነው።

ጌታችን ግን ስለነገም ቢሆን አትጨነቁ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋልና ይለናል ማቴ 6 ቁ28። የነገ ጭንቀት ማለት ወደፊትን የሚያጠቃልል ነው። ዛሬን ተጠንቅቃችሁ በቅድስና በፍጹም እምነት፤ በጸሎት ኑሩ የነገን የሚያውቅ አባት እርሱ ያስባል። ስለትላንትና ከማሰብ ይልቅ ዛሬን በአግባቡ እንያዘው።

ቅዱስ ጳውሎስ “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥” ፊልጵስዩስ 3:13።

“ስለነገም መጨነቅ የለብንም፡ ነገ ገና አልመጣም፡ ነገ ይሄን አደርጋለሁ ይሄንን እሰራለሁ እያልንም በነገ መመካት የለብንም” ጠቢቡ ሰለሞን “ቀን የሚያመጣው ምን እንደሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ!” ምሳ 27፥1 ይላል።

አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር እኛም ዛሬ ስንጸልየው፤ “ጌታ የነገ እንጀራችንን ስጠን በሉ አይደለም ያለን ፤ የእለት እንጀራችንን በየእለቱ ስጠን ብለን ነው የምንጸልየው።

ሙሴ ምድረበዳ በነበረበት ጊዜ ለሕዝቡ ሲነግር፤ ጅግራ እና መና ስትለቅሙ ለዕለት የሚያስፈልጋችሁን ብቻ ልቀሙ ለነገ አዘጋጃለሁ ብሏል አላቸው።  አንዳንዶቹ ነገ አይታወቅም ብለው እምነቱን ተጠራጥረው አብዝተው ለቀሙና ሻገተ፤ ነገር ግን ነገም ዘነበ፤ እየተጠራጠሩ ይለቅሙ ነበር፡ እግዚአብሔርም ከሰማይ መና በየቀኑ ማውረዱን ቀጠለ የሰው ልጅም መጠራጠሩን ቀጠለ።

ፈጣሪ ለችግራችን መፍትሄ ያዘጋጃል፤   ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ፦ “ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” ማር 9፥23 የሚያምን ሰው ሁሉንም ማድረግ ይችላል። ጌታም ይህንን ሲያስረግጥልን፦ ሽክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ፤ ማዕበል ያናወጣችሁ ወደኔ ኑ “እኔ አሳርፋችኋለሁ፤ እንዲያውም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 23 ላይ እንዳለው፦ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል። ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና አልፈራም። ይላል። ይህን እምነት እንያዝ።

እግዚአብሔር በቃሉ የታመነ ነው። ይለናል ቅ. ጳውሎስ 10፡23።

 

 

Previous
Previous

እንኳን ለ2014 ቅዱስ ዮሐንስ አደረሰን።