እንኳን ለ2014 ቅዱስ ዮሐንስ አደረሰን።

እንኳን ለአዲስ አመት በሰላምና በጤና አደረሰን።

ዘመነ ማቴዎስ፤ ዘመነ ማርቆስ፤ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ ሁሉም አውደ አመት ተብሎ ይከበራሉ።

በክርስቲያን ይህን በዓል ቅዱስ ዮሐንስ ብለን ነው የምንጠራው። ዮሐንስ የስሙ ትርጓሜ ጸጋ እግዚአብሔር (የእግዚአብሄር ጸጋ ማለት ነው) ። በዚህ ዘመን ጸጋውን ያልብሰን።

ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍልን የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመርያ እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልዕክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ድምጽ ተብሎ በኢሳይያስ እንደተነገረ የነብዩ የዘካርያስ ልጅ መጥምቁ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመርያ ተነስቶ መንግስተ ሰማይ ቀርባለችና ንሰሐ ግቡ እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንሰሐ ጥምቀት እያጠመቀ ስለ ሃጢያት ሥርየት እየሰበከ መጣ ብሎ ይህንን ትልቅ አስተምህሮ ወንጌላዊው ያስተምረናል።

የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ብሉይ ኪዳን አልፎ አዲስ ኪዳን ሲገባ፤ አዳኝ ከመምጣቱ በፊት ያዘጋጀን ዘንድ የተላከ አዋጅ ነጋሪ ነብይ ነው።  

ቅዱስ ዮሐንስ በአዲስ አመት መጀመርያ ላይ የሚከበርበት ታላቁ ምክንያት፤ ከላይ የተጠቀሰውን መልዕክት ለማስተላልፍ እና የሰው ልጅ እንዲዘጋጅ፤ አካሄዱን ከእግዚአብሄር ጋር እንዲያደርግ፤ ሕይወቱን እዲያቀና፤ ንስሐ እንዲገባም ነው።
አባቶቻችን አዲስ አመት በርሱ ስም እንዲጠራ ያደረጉበት ምክንያት አዲሱን ዘመን በአዲስ አኗኗር፤ በአዲስ መንፈስ፤ በተዘጋጀ ልብ ተቀብለነው እንኖር ዘንድ ነው።

በርግጥ መስከረም ሁለት መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበትንም ቀን እናከብራለን። ይኸውም ጌታችን አስቀድሞ “በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” (ሉቃ1፤14) በማለት የመጥምቁ መወለድ ለእኛ የደስታ ቀናችን መሆኑን ነግሮናል።

ዳግመኛም ጌታችን የመጥምቁን ክብር ሲገልጥለት “እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም” በማለት መስክሮለታል። ማቴ 11፤11።

 መልካም አዲስ አመት ይሁንልን።

Previous
Previous

ዘመጻጒዕ የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት

Next
Next

ከአቅም በላይ የሆነውን ጉዳያችሁን ለርሱ ተውት