solomon asrat solomon asrat

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የልደታ ማርያም ቤተሰቦች - እንኳን ለ2016 ዓ.ም. የሆሳዕና በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። ይህ ታላቅ በዓል ቤተክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት ስታከብረው የቆየ- በክርስትና እምነት ውስጥም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው …

ይህ ታላቅ በዓል ቤተክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት ስታከብረው የቆየ- በክርስትና እምነት ውስጥም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው - እንዲሁም በክርስትና እምነት ውስጥ - ትልቅ አሻራ የሚያሳርፍ በዓል ነው። ይህ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ - የደህንነት ምስጢር ለመፈጸም - ወደ ፍጻሜ የሚገባበትና - ምድራዊ ተልዕኮውን ለማጠናቀቅ - ወደ እየሩሳሌም የሚያቀናበት ታላቅ ዕለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መልኩ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ - በእርግጥም ለምን ዓላማ እንደሚገባና - በዛም የሚያጋጥመውን ሁሉ በሚገባ ያውቃል - ይህንንም የማቴዎስ ወንጌል 20፥17 ጀምሮ በዝርዝር ያስቀምጣል።

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የልደታ ማርያም ቤተሰቦች - እንኳን ለ2016 ዓ.ም. የሆሳዕና በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ።

ይህ ታላቅ በዓል ቤተክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት ስታከብረው የቆየ- በክርስትና እምነት ውስጥም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው - እንዲሁም በክርስትና እምነት ውስጥ - ትልቅ አሻራ የሚያሳርፍ በዓል ነው። ይህ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን ዓላማ - የደህንነት ምስጢር ለመፈጸም - ወደ ፍጻሜ የሚገባበትና - ምድራዊ ተልዕኮውን ለማጠናቀቅ - ወደ እየሩሳሌም የሚያቀናበት ታላቅ ዕለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መልኩ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ - በእርግጥም ለምን ዓላማ እንደሚገባና - በዛም የሚያጋጥመውን ሁሉ በሚገባ ያውቃል - ይህንንም የማቴዎስ ወንጌል 20፥17 ጀምሮ በዝርዝር ያስቀምጣል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም መንገድ ከመጀመራቸው በፊት - 12ቱን ሐዋርያቶች ለብቻቸው ጠርቶ - እንግዲህ አሁን ወደ እየሩሳሌም እንወጣለን - የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፊዎች ተላልፎ ይሰጣል-  እነሱም የሞት ፍርድ የፈርዱበታል - አሳልፈውም ለአሕዛብ እንዲዘባበቱበት - እንዲገርፉትና - እንዲያሰቃዩት - በስተመጨረሻም እንዲሰቅሉት አሳልፈው ይሰጡታል - ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ግን- በ3ኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ - የጨለማውንም ሃይል ሁሉ ረግጦ ይነሳል ብሎ ነግሮአቸዋል።

ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም በሚሄድበት ጊዜ - ዓላማና ግቡን በልቡ ይዞ - ሰለሚመጣው መከራና ስቃይ አምኖበት - የመጣበትን የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም - ወደ ታላቋ ከተማ ወደ እየሩሳሌም - ወንድሞቹን አስከትሎ ተጓዘ። በ1ኛ ቆሮንጦስ 15፥ 36 በተጻፈው መሰረት - ማንኛውም የሚዘራ ፍሬ ካልሞተ ፍሬ እንደማያፈራ - ካልሞተ ሕይወት እንደማይኖረው በመገንዘብና - የእርሱ ሞት ለአሕዛብ ሁሉ - የዘለዓለማዊ ሕይወት ምንጭ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት - የእርሱ ሞት ለአሕዛብ ሁሉ ዘለዓለማዊ ደህንነት የሚያመጣ መሆኑን ስለሚያውቅ - ሕይወቱን ስለ በጎቹ ሲል ለመስጠት - የመጨረሻውን ሰዓት ምድራዊ ጉዞውን ጀመረ ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ - ይህ በአህያይቱ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም የመግባቱ ትንቢት - አስቀድሞ በትንቢተ ዘካርያስ 9፥9 ላይ የተተነበየ - መፈጸምም የሚገባው የቡልይ ኪዳን ትንቢት ሲሆን - ቃሉም እንዲህ ይላል።  አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ - አንቺ የእየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ - እነሆ ንጉስሽ ጻድቅና አዳኝ ነው - ትሁትም ሆኖ - በአህያይቱም ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ - ወደ አንቺ ይመጣል ይላል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም ንጉሥ ሆኖ ሲገባ-  ንግሥናው ዓለማዊ ባለመሆኑ - በሰንጋ ፈረስ ወይም በሰረገላ ላይ ሆኖ ሳይሆን - የትህትና እና የልፋት ምሳሌ በሆነችው - በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ነበር።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም የሚገባበትን - ማንም ሰው ያልተቀመጠባትን ውርንጭላ እንዲያመጡለት - ከደቀመዛምርቱ ሁለቱን ልኳቸው እንደነበር - የማቴ. ወንጌል 21፥2 ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን። ሁላችንም እንደምናውቀው - በቡሉይ ኪዳን ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ሁሉ - በኩር የሆነና- ከእህልም ከሆነ - የመጀመሪያው  ፍሬ መሆን እንዳለበት - በኦሪት ዘሌዋውያን እንዲሁም በሌሎቹም የኦሪት መጻሕፍት ላይ ተዘርዝሮ አናገኘዋለን። በተመሳሳይ መንገድ - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን ራሱን መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ - ወደ መስዋዕቱ ቦታ እየተጓዘ በመሆኑ - ማንም ሰው ያልተቀመጠባት ውርንጭላ ማስፈለጉ ሰለዚህ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የበኩር ልጅ ነው - ከዛም በላይ ራሱ ፍጹም አምላክ ነው - ስለዚህ ይህ የበኩር እና ፍጹም የሆነው አምላክ - ራሱን ለሰው ልጆች ደህንነት - ለመስዋዕትነት ለማቅረብ ሲጓዝ - ይህን የተቀደሰ መስዋዕት ይዞ የሚጓዘው እንስሳም - ንጹህ መሆን ስለነበረበት - ይቺ ማንም የልተቀመጠባት ውርንጭላ አስፈለገች። ይህ ሁሉ የሚያመላክተን - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቡልይ ኪዳን - ስለእርሱ የተጻፉትን ትንቢቶች ሁሉ - አንድም ሳያስቀር በምድራዊ ሕይወቱ ተግብሯቸዋል - ለዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቡልይ ኪዳን ፍጻሜ በእርሱ ተከናወነ - እርሱ የቡልይ ኪዳን መደምደሚያ - የአዲስ ኪዳን ደግሞ መክፈቻ ቁልፍ ነው ብለን የምንመሰክረው።

ደቀመዛምርቱ የአህያዋን ውርንጭላ ካመጡለት በኋላ-  ልብሳቸውን በአህያዋ ውርንጭላ ላይ አነጠፉ- ይህም ለእርሱ ታዛዢ መሆናቸውንና - እርሱንም እንደ ንጉስ መቀበላቸውን የሚያመሳክር ነበር። ኢየሱስም በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ - ወደ እየሩሳሌም በታላቅ እልልታና ደስታ ሲገባ - ብዙ ሰዎች ደስታቸውን ለመግለጽ - አንዳንዶቹ ልብሳቸውን በመንገዱ ላይ በማንጠፍ - ሌሎቹ ደግሞ የደስታና የድል ምልክት የሆነውን - የዘንባባ ዝንጣፊ በመሬቱ ላይ ይጎዘጉዙ ነበር። እንዲሁም በዛ የተገኙትም ሁሉ - ሆሳዕና በአርያም - በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው - ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ - ሆሳዕና ለኢየሱስ - ሆሳዕና ለክርስቶስ በማለት - በታልቅ ድምጽ ይጮሁ ነበር።

ሆሳዕና ማለት የእብራይስጥ ቃል ሲሆን - ቀጥተኛ ትርጉሙ - መዳን ወይም አዳኝ በሚለው ሊተረጎም ይችላል። በዛን ጊዜ በዙሪያው የነበሩት ሰዎች - ይህ ሁሉ ደስታቸውና እልልታቸው - ምን አልባት እነሱ ይጠብቁት የነበረው ነቢይ - ከሮማውያኑ አገዛዝ ነጻ የሚያወጣቸው ነቢይ - እንደ ሳኦልና ዳዊት - እንደ ንጉስ ሰሎሞን - እስራኤላውያኑን በዙሪያቸው ካሉ ጠላቶቻቸውና - ጫና ከሚያሳድሩባቸው የአካባቢው ገዢዎች - ነጻ የሚያወጣ -የሚያድናቸው ነቢይ አድርገው ስለውትም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በእርግጥም እነሱ ሙሉ በሙሉ አይረዱት እንጂ - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም በአህያይቱ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ መግባቱ - የሰውን ልጅ ሁል ጊዜም ከሚያስጨንቀውና - ጨቁኖ ከያዘው - የእግዚአብሔር ልጅነትን ጸጋ ከሚያሳጣው  ኃጢአትና - ከዲያቢሎስ እስር  ነጻ ሊያወጣው  - ከዘለዓለማዊ ሞት ሊያድነው የመጣ ነቢይ ነው። ይህንንም በትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 61 - ላይ ለድሆች የምስራችን እሰብክ ዘንድ - ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ - ለተማረኩትም ነጻነትን - ለታሰሩትም መፈታትን  አውጅ ዘንድ - የሚያለቅሱትንም እንዳጽናና - በለቅሶም ፈንታ የደስታን ዘይት -  በኃዘን መንፈስም  የመጽናናት መጎናጸፊያን እንደሰጥ ልኮኛል በሚለው ቃሉ ይገልጸዋል።

በሉቃስ ወንጌል 21፥39 ላይ - ከፈሪሳውያኑ ወገንና መምህር የነበሩት - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማሳደድና ለማስወገድ ያሴሩ የነበሩት - ደቀመዛምርቱን - እንዲሁም በእልልታና በሆታ ያጀቡትን ሕዝቡን ሁሉ - ዝም እንዲያሰኝ እንደነገሩት ይነግረናል - ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ - እነሱ ዝም ቢሉ እንኳን - ድንጋዮች ይጮሃሉ ብሎ መልሶላቸዋል። ይህም የሚያሳየን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስበኃይሉና በስልጣኑ - አውሎ ነፋስን ጸጥ የሚያሰኝ - ታላላቅ የባሕር ወጀቦችን የሚገስጽ - ሽባውን የሚተረትር - የጎበጠውን የሚያቀና - የጠፋውን ዓይን የሚያበራ - ለሞተዉም መልሶ ነፍስን የሚዘራ - በቃሉ ብቻ ዓለማትን የፈጠረ - ዓለምና በእርሷ ውስጥ ያሉት ሁሉ የሚታዘዙለት - አቻ የሌለው አምላክ መሆኑን ነው።

የዛሬው የዕብራውያን መልዕክት - ከምዕራፍ 9 ላይ ያነበብነው - በብሉይ ኪዳን ዘመን ይካሄድ እንደነበረው - ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት እንዲቀርቡ - ለኃጢአታቸው ካሣ የሚሆን - በካህኑ አማካኝነት ታርዶ የሚቃጠለው  ኮርማና ፍየል - የሚረጨውም የእንስሳቱ ደም  - ከእንግዲህ ወዲህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስደም እንደተተካ ይነግረናል።የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስመስዋዕት ፍጹም ነው - በመሆኑም እንደ እንስሳቱ ደም - በየጊዜው የሚታረድና የሚረጭ ሳይሆን - በመስዋዕቱ - ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ - የሰውን ልጅ ሁሉ - ዘለዓለማዊ ደህንነትን የሚያጎናጽፍ ነው።

ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቱ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም የሚጓዘው - የሁላችንን የኃጢአት እዳ ለመክፈል ነው - እኛን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ሊያወጣን ነው - ያውም ለአንድና ሁለት ጊዜ ሳይሆን - ለዘለዓለሙ ሊቤዤን ነው። በጀመሪያዎቹ በቡልይ ኪዳን ዘመናት - የእግዚአብሔር ማደሪያው - የቃል ኪዳኑ ድንኳን ነበር - ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መስዋዕት በደሙ ከከፈለልን በኋላ ግን - የእግዚአብሔር ማደሪያ - የቃል ኪዳኑ ድንኳን ሳይሆን - የእያንዳዳችን ሰውነት ነው። ይህንንም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ምዕራፍ 12፥1 ላይ ሲያረጋግጥልን እንዲህ ይለናል - ወንድሞችና እህቶች ሆይ - እንግዲህ ሰውነታችሁ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና - ሕያው - ቅዱስም መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ - በእግዚአብር ርህራሄ እለምናችኋለው ይለናል።

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም የታጠበው - የተቀደሰው ሰውነታችን - ዘለዓለማዊ ደህንነትን የተጎናጸፈው እኛነታችን - ይህን ቅድስናውንና - ንጽህናውን ይዞ መቀጠል የሚችለው  -ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይዞ መጓዝ እስከቻለ ጊዜ ብቻ ነው። ይህንንም አብሮነት ለማስቀጠል - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምስጢራት አማካኝነት መንገዱን አበጅቶታል - ስለዚህ ይበልጥ ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስየሚያቀራርበንን - ምስጢረ ንስሃና ምስጢረ ቁርባን - አዘውትረን በመቀበል - ይህንን ከእርሱ ጋር ያለንን አንድነታችንን እናጠናክር። ይህንን እውነታ ወንጌላዊው ዮሐንስ 15፥4 ጀምሮ እንዲህ ይገልጸዋል - በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ - ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር- በራሱ ምንም ዓይነት ፍሬ ማፍራት እንደማይችል ሁሉ - እናንተም በእኔ ባትኖሩ - ምንም ማድረግ አትችሉም - እኔ የወይን ግንድ ነኝ - እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ - ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና - በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ እኖራለሁ - ብዙ ፍሬም ያፈራል ይለናል። ስለዚህ የወይኑ ግንድ ከሆነው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ህብረታችን ካልጠነከረ - በህይወታችን ምንም ዓይነት መልካም ፍሬ ልናፈራ አንችልም።

ዛሬ በ2ኛ መልዕክት ከ1ኛ ጴጥ. 4 ላይ ያነበብነውም-  ከዚሁ ሃሳብ ጋር የሚስማማ መልዕክት ይነግረናል - እንዲህም ይለናል - እንግዲህ በስጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን - እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጅ - እንደ ሰው ምኞት አትኑሩ ይለናል። ሰው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖር - የረጋ አይምሮ ያስፈልገዋል - በተረጋጋ አእምሮ ከክርስቶስ ጋር ሕብረቱን ካቆመ - ባልእንጀራውን እንደ ራሱ መመልከት - ከእግዚአብሔር በተቀበለውም ጸጋና- ከእርሱ በሚመነጨው ኃይልና ብርታት - እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ መመላለስ - በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ቤት - ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የከፈለለትን  ዘለዓለማዊ ሕይወት መቋደስ ያስችለዋል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንድንችል - ከልደቱ እስከ ትንሣዔው አብራው የተጓዘችው እናቱ እመቢታችን ቅድስት ድንግል ማርያም - ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ - ይህንን የሆሳዕና በዓል በረከትና ጸጋ ለእያንዳዳችን ታሰጠን - በዓላችንን የበረከትና ብዙ- መንፈሳዊ ጸጋ የምንሰብስብበትም ያድርግልን።

Read More
solomon asrat solomon asrat

ዘመጻጒዕ የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት

የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት ዘመጻጒዕ ተብሎ ይጠራል፤ ይህም የሕመሙማን ፈውስ ሰንበት፣ የመነካት ሰንበት፣ የነጻነት ሰንበት እና ከደዌ የመፈታት ሰንበት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዛሬው ክፍል ኢየሱስ ቤተ-ሳይዳ ወደምትባል አምስት መመላለሻዎች ወዳሏት መጠመቂያ ስፍራ እንደመጣ ይናገራል።

ዘመጻጒዕ የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት

ንባባት፡- ገላ 5፡ 1-26፣ ያዕ 5፡14-20፣ ሐዋ 3፡1-11

ስብከት፡- “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዓራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኲሎ ምስካቢሁ እምደዌሁ፤ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፤ እኔስ አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ” (መዝ 41፡3-4) ።

ወንጌል፡- ዮሐ 5፡ 1-24

የዐቢይ ጾም ፬ኛ ሰንበት ዘመጻጒዕ ተብሎ ይጠራል፤ ይህም የሕሙማን ፈውስ ሰንበት፣ የመነካት ሰንበት፣ የነጻነት ሰንበት እና ከደዌ የመፈታት ሰንበት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዛሬው ክፍል ኢየሱስ ቤተ-ሳይዳ ወደምትባል አምስት መመላለሻዎች ወዳሏት መጠመቂያ ስፍራ እንደመጣ ይናገራል። ኢየሱስ ወደዚህ ሥፍራ መምጣቱ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ዓላማ ምሥጢር በትክክል የሚተረጉምልን ቁልፍ ተግባር ነው። ኢየሱስ ወደዚህ ስፍራ ሲመጣ “በበጎች በር” (ዮሐ 5፡2) በኩል እንደነበረ ቅዱስ ዮሐንስ ይናገራል።  ይህ “በበጎች በር” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የብሉይ ኪዳን ካህናት በዚያ በር አጠገብ ለመሥዋዕት የሚቀርቡትን በጎች መርጠው፣ አጥበው የሚሸልቱበትን ሥፍራ መሆኑ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ወደዚህ በር መምጣቱ ወደሚታረድበት መንበረ ታቦት እና መሥዋዕት ለመሆን ወደሚዘጋጅበት መቅደስ መቅረቡን የሚያመላክት ነው።

ነገር ግን የእነዚህ በጎች ንጽህና እና መሥዋዕት ሆነው መቅረባቸው ለዓለም ሁሉ መዳን ሊያመጣ አልቻለም። ዓለም ከእነዚህ በጎች ደም ይልቅ በከበረ እና ንጹህ በሆነ ደም መታጠብ ነበረባት! መጥምቁ ዮሐንስ ይህንን አውቆ ስለነበረ ኢየሱስን ለዓለም ሲያስተዋውቀው “የዓለምን ኃጢአት የሚያጠፋ የእግዚአብሔር በግ እነሆ” (ዮሐ 1፡29) ይላል። በብሉይ ኪዳን ዘመን አብርሃም በልጁ ፈንታ ይሠዋው ዘንድ ቀንዶቹ በሐረግ የተያዘውን በግ እያስታወሰ በይስሐቅ ፈንታ የሚሰዋው እውነተኛ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሆኑን ይመሰክርልናል። የሀገራችን ሥርዐተ አምልኮ ይህንን ተከትሎ የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ላይ በምናቀርበው ምልጣን “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሃጺባ በደመ ክርስቶስ” እያልን እንዘምራለን። ስለዚህ ኢየሱስ በበጎች በር አጠገብ ቆሞ መመልከታችን የእንስሳት ደም መሥዋዕት ማብቃቱን እና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈሰው፣ ዓለምን ሁሉ የሚፈውሰው፣ ሰማይንና ምድርን አዲስ ያደርግ ዘንድ ምድር በአዲስ ልደት የምትታጠብበት የደም ጥምቀት የሚፈጸመበት ዘመን መምጣቱን የሚያሳይ ነው! በመሆኑም ምድር በእንስሳት ደም ሳይሆን በኢየሱስ ደም ታጥባ ፋሲካዋን ታከብራለች።

በመቀጠልም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ ሳይዳ የመጠመቂያ ስፍራ መኖሩን ይናገራል። በዚህም ሥፍራ ከጊዜ ወደ ጊዜ መላእክት ወርደው ውኃውን እንደሚያናውጡት እና ውኃው ከዚህ የተነሳ የሚፈውስ ውኃ እንደሚሆን፣ ከመላእክቱ መውረድ የተነሳ የመለኮታዊ ፈውስ በውኃው ላይ እንደሚገለጥ እናነባለን። ነገር ግን የዚህ የቤተ ሳይዳ ውኃ ፈውስ፣ አቅም ላላቸው እና ሰው ላላቸው ለባለ ወገን ብቻ የሚሆን ውኃ ነበር። ኢየሱስ የቤተ ሳይዳውን ውኃ ሳይሆን በደሙ የሚቀድሰውን አዲስ ውኃ ይሰጥ ዘንድ በቤተ ሳይዳ መጠመቂ ሥፍራ ቆሟል። ጌታ ወደዚህ መጠመቂያ ሥፍራ መውረዱ አሁን መላእክት ሳይሆኑ የመላእክት ሁሉ ጌታ ራሱ ወደ ውኃው መውረዱን እና የአዲስ ኪዳን ውኃ የመከፈቱን የምሥራች የሚያበስር ነው። ይህም የምሥጢረ ጥምቀትን ጸጋ የሚያመላክት ሲሆን ኢየሱስ በዚያ መገለጡ እና ፈውስ ማድረጉ ምሥጢረ ጥምቀት ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተከፈተ የመለኮታዊ ምሕረት እና የዳግም ልደት ምሥጢር መሆኑን ያስገነዝበናል። የቤተ ሳይዳ ውኃ በመላእክት ኃይል የሥጋን ደዌ ሁሉ ይፈውስ እንደነበረ ሁሉ የአዲስ ኪዳን የጥምቀት ውኃ በኢየሱስ መለኮታዊ ሥልጣን እና በቅድስት ሥላሴ ስም ነፍስን እና ሥጋን ሁሉ ይቀድሳል፤ የአዲስ ኪዳን ውኃ እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ወንዶች እና ሴቶች ልጆች፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞችና እኅቶች፣ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ሆነን ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን የምንወለድበት የዳግም ልደት ምሥጢር አለው።

በቤተ ሳይዳ ውኃ ሕሙማን ከሥጋ ደዌ ተፈውሰዋል ነገር ግን እኛ በበለጠው በአዲስ ኪዳን ውኃ ከሥጋ ደዌ መፈወስ ሳይሆን ከቅድስት ሥላሴ ጋር የሥጋ ዝምድና አለን። እርሱ ስለወደደን በደሙ አጥቦናልና (ራዕ 1፡5) በዚህ ፍቅር መካከል ከእርሱ እና ከእኛ በስተቀር ንፋስ እንኳን ቢሆን መግቢያ የለውም፤ ምክንያቱም በመካከላችን ያለው ቃልኪዳን ሥጋ ላይ በሚቀር ግርዛት ሳይሆን “ከሞቱ ጋር አንድ በሚያደርግ ጥምቀት ነው” (ሮሜ 6፡3)። ይህም ማለት ኃጢአት አንሰራም፣ አንወድቅም፣ አምላክን አናሳዝንም ማለት ሳይሆን ፍቅሩ ከእኛ ደካም ጋር የሚነጻጸር፣ ፍቅሩ በእኛ ዕለታዊ ማንነት ላይ የተመሰረት እና ተለዋዋጭ አይደለም ማለታችን ነው። እርሱ ካለብን ኃጢአት በላይ እኛን የሚያጸድቅበት ጸጋ፣ ከወረድንበት ሸለቆ በላይ እኛን ከፍ የሚያደርግበት ክብር፣ ከታሰርንበት ሰንሰለት በላይ አርነት የሚያወጣ ቃል፣ ከተበዘበዝንበት ቀንበር በላይ የጫንቃን ቁስል የሚፈውስ ዘይት፣ ከተዋረድንበት አጸያፊ ገጽታ በላይ አዲስ ካባ የሚያለብስበት አባታዊ ልብ አለው ማለታችን ነው። መጽሐፍ ይህንን ሲመሰክርልን እንዲህ ይላል፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናም፣ ዛሬም፣ እስከ ዘላለም ያው ነው!” (ዕብ 13፡8)

ቅዱስ ዮሐንስ የቤተ ሳይዳው መጠመቂያ አምስት በሮች እንደነበሩት ይናገራል። እነዚህ አምስት በሮች ወደ ፈዋሽ ውኃ የሚያስገቡ በሮች ናቸው። ሕሙማን በእነዚህ በሮች ወደ ፈውስ ይመጡ ዘንድ እነዚህ በሮች ተከፍተዋል፤ ነገር ግን በእነዚህ በሮች የሚገቡ ሁሉ ፈውስ ያገኛሉ ማለት አይደለም። በበሮቹ ቢገቡም ወደ ፈዋሽ ውኃው የሚያስገባቸው ወገን ያስፈልጋቸው ነበር። ነገር ግን በእነዚህ በሮች እንገባ እና ወደ ፈዋሽ ውኃ እንደርስ ዘንድ በሮቹ የት አሉ? ዛሬስ የፈውስ በሮች ክፍት ሆነው የሚታዩት የት ነው? ነቢዩ ኢሳያስ ከዘመናት በፊት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” (ኢሳ 53፡5) ይላል።

ስለዚህ እነዚህ አምስቱ የቤተ ሳይዳ የፈውስ በሮች አምስቱ የጌታ ቁስሎች ናቸው። እነርሱ በምስማር እና በጦር ከመከፈታቸው አስቀድሞ በእርግጥ ከዘለዓለም ጀምሮ በፍቅር ኃይል ተክፍተው ነበርና ጌታ “በሩ እኔ ነኝ” (ዮሐ 10፡9) ይላል፤ በእርሱ በኩል እንድንገባ እና እንድንወጣ ብሎም መሰማርያ እንድናገኝ ይጋብዘናል። በእነዚህ በሮች በኩል ወደማይታየው አምላክ መመልከት እንችላለንና ጌታ “እጆቼን እና እግሮቼን እዩ!” (ሉቃ 24፡39) እያለ ወደ ቅድስት ሥላሴ ልብ ትርታ የሚያሳየንን የምሕረት በር ይጠቁመናል። በእርግጥም ዐቢይ ጾም በመስቀል መንገድ የጌታን ቁስሎች የምናስተነትንበት ጉዞ ነው።

ቅዱስ አውጉስጢኖስ እነዚህን የቤተ ሳይዳ በሮች በሚመለከት እነርሱ አምስቱ የሙሴ የሕግ መጽሐፍት ምልክቶች ናቸው ይላል። በመሆኑም አይሁድ በሕግ እንጂ በጸጋ አልነበሩምና ሕግ የነፍስን ቁስሎች ለመፈወስ ስልጣን የለውም። በዚህም በቅዱስ ዮሐንስን የወንጌል ዕውሮች፣ አንካሶች፣ ሰውነታቸውም የሰለለ እየተባሉ በስም የተጠቀሱ የበሽታ አይነቶች ሁሉ ውጫዊ እና አካላዊ ጎዶሎነትን የሚያሳዩ በመሆናቸው ሕግ ሁሉን ሊፈውስ እንደማይቻለው እና ሁሉን እንደማይጠቀልል የሚያመላክት መሆኑን ይገልጻል። የዕብራውያን መጽሐፍ ስለዚህ ሲመሰክር “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና” (ዕብ 10፡4) እያለ አዲሱ ደም የግድ እንደሆነ ያሳየናል። እነዚህን በቤተ ሳይዳ የወደቁ ሕሙማንን ማንሳት እና ሕይወት መዝራት የሚችለው የኢየሱስ ደም ብቻ ነው። ደሙ ያነሳል፣ ደሙ ያጥባል፣ ደሙ ያነጻል፣ ደሙ ይቀድሳል፣ ደሙ ያከብራል፤ ደሙ ዘማዊውን ድንግል ያደርጋል።

እነዚህ ሕሙማን በዮሐንስ ወንጌል የተገለጹበት ሁኔታ ብዙ የሚናገረው ነገር አለው። በመጀመርያ ሕመማኑ “በመሬት ላይ ተኝተው” ነበር የሚለው ስዕላዊ አገላለጽ ኃጢአት በነፍስ ላይ የሚያደርሰውን ቁስል የሚያመለክት ሲሆን፣ ነፍስ በኃጢአት ቀንበር ወደ መሬት ተደፍታ፣ በምድራዊ ነገሮች ተገዝታ እና ተበዝብዛ መድከሟን መመልከት እንችላለን። እንዲህ ያለችው ነፍስ ወደ እግዚአብሔር ቀና ማለት የምትችልበትን የጸጋ ኃይል ስለተነጠቀች ወደ ውኃው የሚጥላትን ሰው ከመጠባበቅ የተለየ ሌላ ተስፋ የላትምና ጌታ በቀረባት ጊዜ “ጌታ ሆይ ሰው የለኝም!” (ዮሐ 5፡7) እያለች ተስፋዋ ሁሉ እንደተሟጠጠ ትናገራለች። ሰው የለኝም! ምሥጢሬን የማሳየው፣ በምሥጢሬ የምታመንበት፣ ቁስሌን የማሳየው፣ በቁስሌ መክፋት የማይጠየፈኝ፣ የማለቅስበት፣ የዕንባዬን ዋጋ እና የተስፋ መቁረጤን ጥግ የሚያውቅልኝ ሰው የለኝም! ለተወሰነ ጊዜ የሕይወታችንን ጉዞ ብናስተውለው ይህ “ሰው የለኝም!” የሚለው የቤተ ሳይዳው ሰው ዋይታ የእያንዳንዳችን መሆኑን መመልከት እንችላለን።

ዛሬ ቁስላችንን፣ የምናፍርባቸው የሕይወት ገጠመኞቻችንን፣ የወደቅንባቸው፣ የተማረክንባቸው ኃጢአቶቻችንን የምናዋየው ሰው ማነው? ለማን ነው ልባችንን አምነን መክፈት የምንችለው? ለራሳችን እንኳን ልናስበው ሰላም የሚነሳንን እና የሚያሸማቅቀንን ነገር አውጥተን የምንነግረው ሰው ይኖረን ይሆን? ወይስ ከቤተ ሳይዳው ሰው ዋይታ ተውሰን እኛም “ጌታ ሆይ ሰው የለኝም!” እንላለን? ነገር ግን አዲስ ኪዳን የሚያጽናና መለኮታዊ የምሥራች አለው፤ ይኸውም ሰው እንደሌለን የሚያወቅ፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች መቅበዝበዛችንን (ማቴ 9፡36፤ ማር 6፡34) ያየው ኢየሱስ ይህንን አውቆ ሰው ለሆንልን ሰው ሆኗል! ስለዚህ ወደ እኔ ቀርቦ “መዳን ትወዳለህን” (ዮሐ 5፡7) እያለ እጁን ይዘረጋልኛል።

እርሱ የእኔን የተዋረደ ሥጋ ገንዘቡ አድርጎ “የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ” (ፊል 2፡7-8) ስለዚህ ከዚህ በላይ የሚያጸይፈው፣ ከእኔ የሚያሸሸው፣ የቁስሌ ሽታ የማያስጠጋው ኃጢአት የለም። ስለዚህ ጌታ ዛሬም ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል፤ ወደ ወረድንበት ሸለቆ ጥግ፣ ወደ ተያዝንበት የአለት ንቃቃት ስር፣ የአሳማ ምግብ እስከ መጎምጀት ክብራችንን ወደተገፈፍንበት ባርነትና ኃጢአት ይመጣል! እርሱ ለእያንዳንዳቸን ሊያደርግ የሚፈልገውን ነገር ነቢዩ ኤርሚያስ ሲናገር “በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል፡-ቀንበርህን ከአንገት እሰብራለሁ፤ እሥራትህንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ለሌላ አትገዛም” (ኤር 30፡8) እያለ ተስፋ ይሰጠናል።

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ትረካውን ቀጥሎ በቤተ ሳይዳ የመጠመቂያ ሥፍራ የነበሩትን ሰዎች ሁኔታ እያብራራ፣ አንደኛ ከሕሙማኑ መካከል ገሚሱ “ሰውነታቸው የሰለለ” እንደነበር ይናገራል። ይህ የዮሐንስ አገላለጽ በፍትወት ኃጢአት የምትሰቃይ ነፍስ ያላትን አካላዊ ገጽታ የሚያመለክት ሲሆን ሥጋ ከፍትወቱ እና እርሱንም ከሚያሟላበት ነገር ውጭ ሌላ ምንም ነገር ማድረግ በማይችልበት፣ የነፍስ ኃይላት በዚህ ያልተገራ ሥጋዊ ፍትወት የተጠመዱበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ንጽሕና ሲጎድል የሰውነት ሰው ሆኖ በምልዐት የመገለጥ ኃይል ይጎድላል፤ ንጽሕና የጉልምስናን ዘመን እንደ ንሥር ወጣት አድርጎ ያድሳል።  በመቀጠልም በሁለተኛ ደረጃ ዕውራን በዚያ እንደነበሩ ዮሐንስ ይናገራል። ዮሐንስ ዕውራን የሚላቸው ማየት የተሳናቸውን፣ ውጫዊ የሆነ አካላዊ የማየት አቅም የሌላቸውን ብቻ ሳይሆን ያልተገራ ፍትወት የሚሰለጥንበትን  አዕምሮ ጭምር ነው። መጽሐፈ ጥበብ 2፡21 “ምክንያቱም እነርሱ እንደዚህ አሰቡ በዚህም ሳቱ፤ ጥላቻቸው አሳውሯቸዋል” እያለ ዕውርነት ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዘ መሆኑን ያሳተምረናል። ዕውርነት የነፍስ የማስተዋል ብርኀን መደብዘዝ ነው። ሰውነቱ የሰለለ እና የታወረ ሰው ጸንቶ መቆም ስለማይችል እና ጸንቶ የሚቆምበት ቅጥር እና መልህቅ ሰለሌለው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ይህንን የሰው ልጅ ሁኔታ “ሽባነት” እያለ ይገልጸዋል።

በዚህ የወንጌል ክፍል የምናስተውለው የሕሙማኑ ሁኔታ ለመንፈሳዊ ሕይወት ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ቁም ነገር ያስተምረናል፤ ቅዱስ ዮሐንስ የሕሙማኑን ሁኔታ ሲገለጽልን “የውኃውን መናወጥ የሚጠባበቁ” ነበሩ ይላል። ፈውስን መናፈቅ እና ፈውስን መጠበቅ ለመዳን ቁርጥ ፈቃድ ማድረግ የሚጠይቅ ተግባር ነው። መጠበቅ እምነትን፣ ተስፋን እና ፍቅርን ይጠይቃል። ዛሬ የምንገኝበት የዐቢይ ጾም ወቅት የጸጋ ወቅት ነው፤ የመሲሁን ሕማም እና ሞት በእውነት እና በመንፈስ እየተካፈልን ፈውስ ሁሉ የሚገኝበትን ትንሳኤውን የምንጠባበቅበት የጸጋ ዘመን፣ የተወደደው የጌታ ዓመት ዛሬ ነው።

ትልቁ ኃጢአት በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ መቁረጥ ነው! ስለዚህ ውኃውን ሳይሆን ደሙን በተስፋ እየጠበቅን ደግሞም በመካከላችን በምሥጢረ ቊርባን የደሙን ዋጋ እያከበርን፣ እርሱን እንመስል ዘንድ ከሥጋው እየበላን እና ከደሙ እየጠጣን እንጠብቅ! ከእምነት አባታችን ከያዕቆብ ጋር እግዚአብሔርን በእምነት እየታገልን እና ካልባረከኝ አልለቅህም እያልን መድኃኒትን እንጠብቅ!

ነገር ግን እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ሌላ ቁም ነገር አለ። የቤተ ሳይዳው ሰው ጌታ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ የሚያስደንቅ ምላሽ ነው፤ ጌታ “ልትድን ትወዳለህን?” ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ ሰላሳ ስምንት ዓመት በዚያ ሁኔታ ሲሰቃይ የነበረው ሰው “ጌታ ሆይ ወደ ውኃው የሚጥለኝ ሰው የለኝም!” እያለ የራሱን የመዳን መርሐ ግብር ለጌታ ይናገራል። ምናልባት የዚህ ሰው ታሪክ ወደ ብሉይ ኪዳን ተመልሰን ለምጽ የመታውን ታላቁን የሶርያ ንጉሥ ንዕማንን እንድናስታውስ ይጋብዘናል። ንዕማን ፈውስ ፍለጋ ሀገር አቋርጦ ወደ ነብዩ ኤልሳዕ ሲመጣ  ከለምጹ ይፈወስ ዘንድ ነቢዩ ኤልሳዕ በዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ሰባት ጊዜ እንዲታጠብ በነገረው ጊዜ “ንዕማን ግን ተቆጥቶ ሄደ፤ እንዲህም አለ፡- እነሆ ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን  ስም የሚጠራ፣ የለምጹንም ሥፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር!። የደማስቆ ወንዞች አባርናና ፋርፋ ከእሥራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱም ውስጥ መታጠብ እና መንጻት አይቻለኝም ኖሯልን?” (2ኛ ነገ 5፡11-12) ንዕማን ፈውስ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚፈወስ ጭምር የራሱ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። ይህ አይነቱ ለራስ መድኃኔዓለም የመሆን ፍላጎት በእግዚአብሔር ዘንድ ሥፍራ የለውም። ዐቢይ ጾም የመሰራት፣ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የመፈወስ እና እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ፣ በእግዚአብሔር ሐሳብ፣ ለእግዚአብሔር ሐሳብ የመለወጥ ጉዞ ነው። ዛሬ ጌታ መዳን ትወዳለህን? በሎ ለሚያቀርብልን ጥያቄ ከእመቤታችን ትህትና እና እምነት ጋር ተባብረን “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ እንዳንተ ፈቃድ ይሁንልኝ!” የምንልበት የጾም ወቅት ይሁንልን!

"እርሱ ካለብን ኃጢአት በላይ እኛን የሚያጸድቅበት ጸጋ፣ ከወረድንበት ሸለቆ በላይ እኛን ከፍ የሚያደርግበት ክብር፣ ከታሰርንበት ሰንሰለት በላይ አርነት የሚያወጣ ቃል፣ ከተበዘበዝንበት ቀንበር በላይ የጫንቃን ቁስል የሚፈውስ ዘይት፣ ከተዋረድንበት አጸያፊ ገጽታ በላይ አዲስ ካባ የሚያለብስበት አባታዊ ልብ አለው ማለታችን ነው።"

"ዐቢይ ጾም የመሰራት፣ እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የመፈወስ እና እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ፣ በእግዚአብሔር ሐሳብ፣ ለእግዚአብሔር ሐሳብ የመለወጥ ጉዞ ያድርግልን"

Read More
solomon asrat solomon asrat

እንኳን ለ2014 ቅዱስ ዮሐንስ አደረሰን።

እንኳን ለአዲስ አመት በሰላምና በጤና አደረሰን።

ዘመነ ማቴዎስ፤ ዘመነ ማርቆስ፤ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ ሁሉም አውደ አመት ተብሎ ይከበራሉ።

በክርስቲያን ይህን በዓል ቅዱስ ዮሐንስ ብለን ነው የምንጠራው። ዮሐንስ የስሙ ትርጓሜ ጸጋ እግዚአብሔር (የእግዚአብሄር ጸጋ ማለት ነው) ። በዚህ ዘመን ጸጋውን ያልብሰን።

ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍልን የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመርያ እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልዕክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ድምጽ ተብሎ በኢሳይያስ እንደተነገረ የነብዩ የዘካርያስ ልጅ መጥምቁ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመርያ ተነስቶ መንግስተ ሰማይ ቀርባለችና ንሰሐ ግቡ እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንሰሐ ጥምቀት እያጠመቀ ስለ ሃጢያት ሥርየት እየሰበከ መጣ ብሎ ይህንን ትልቅ አስተምህሮ ወንጌላዊው ያስተምረናል።

የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ብሉይ ኪዳን አልፎ አዲስ ኪዳን ሲገባ፤ አዳኝ ከመምጣቱ በፊት ያዘጋጀን ዘንድ የተላከ አዋጅ ነጋሪ ነብይ ነው።  

ቅዱስ ዮሐንስ በአዲስ አመት መጀመርያ ላይ የሚከበርበት ታላቁ ምክንያት፤ ከላይ የተጠቀሰውን መልዕክት ለማስተላልፍ እና የሰው ልጅ እንዲዘጋጅ፤ አካሄዱን ከእግዚአብሄር ጋር እንዲያደርግ፤ ሕይወቱን እዲያቀና፤ ንስሐ እንዲገባም ነው።
አባቶቻችን አዲስ አመት በርሱ ስም እንዲጠራ ያደረጉበት ምክንያት አዲሱን ዘመን በአዲስ አኗኗር፤ በአዲስ መንፈስ፤ በተዘጋጀ ልብ ተቀብለነው እንኖር ዘንድ ነው።

በርግጥ መስከረም ሁለት መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበትንም ቀን እናከብራለን። ይኸውም ጌታችን አስቀድሞ “በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” (ሉቃ1፤14) በማለት የመጥምቁ መወለድ ለእኛ የደስታ ቀናችን መሆኑን ነግሮናል።

ዳግመኛም ጌታችን የመጥምቁን ክብር ሲገልጥለት “እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም” በማለት መስክሮለታል። ማቴ 11፤11።

 መልካም አዲስ አመት ይሁንልን።

Read More
solomon asrat solomon asrat

ከአቅም በላይ የሆነውን ጉዳያችሁን ለርሱ ተውት

 

እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው። በተፈጠሩ ወይንም በፈጠራቸው ነገሮች ሁሉ የበላይ ገዢ ነው። ይህንን እናውቃለን እናምናለንም።

በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ቁ 48 ላይ እንደተጻፈልን፣ ደቀመዛሙርቱ በባሕር ላይ ሆነው ሲጓዙ በነፋስ ማዕበል ምክንያት መቅዘፍ አቅቷቸው  በተጨነቁ ሰዓት ኢየሱስ ክርስቶስ በርጋታ ውኃው ላይ እየተራመደ ሄዶ እነርሱ በነበሩበት ጀልባ ላይ  ሲወጣ ማዕበሉ እንደቆመ ይነግረናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየተራመደ የመጣው እኛ ችግር ነው ልናልፈው አንችልም የምንለው እክል ላይ ነው፤ አስቸጋሪ ጉዳያችን ላይ ነው፤ ለእኛ ከአቅም በላይ ነው ባልነው ነገር ላይ ነው። ደቀመዛሙርቱ የተሰቃዩት በማዕበሉ የመጣ ነው፣ ክርስቶስ ደሞ በዚያው ችግር በሆነው ማዕበል ላይ ነው እየተራመደ የመጣው።

እስቲ ወደራሳችን ማዕበል መለስ ብለን እናስተውል።  ዛሬ እኔና እናንተ ፊት ያለው ማዕበል ምንድነው? ይህ የሕይወቴ ማዕበል ነው የምንለው ነገር አለ? የቤተሰብ ሃሳብ፤ የልጆች ጉዳይ? የጤና መታወክ፤ ኢኮኖሚ፤ ሥራ ማጣት፤ አለመመቻቸት፤ የትዳር ጉዳይ? አጠቃላይ የሕይወት ውጣ ውረድ የሆነብን ማዕበል፤ ፊታችን ያለው ጦርነት፤ ዘወትር የምንሰማው በሽታ፤ ወረርሽኝ፤ ረሃብ፤ ፈጣሪያችን ከነዚ ማዕበል በሙሉ በላይ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስ በገላቲያ ለተሰደዱት ክርስቲያኖች 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፥7 ላይ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት ብሎ ነግሯቸዋል ።

ጭንቀት የሚፈጠረው ከአቅማችን በላይ ስናስብ ጭምር ነው፣ ከአቅም በላይ የሆነውን ጉዳያችሁን ለርሱ ተውት ይላል ቅዱስ ጴጥሮስ። የሚያስጨንቀን ከአቅማችን በላይ ከሆነ ማረፍ የምንችለው በእርሱ ላይ የመጣል ፍጹም እምነት ሲኖረን ነው።

ጌታችን ግን ስለነገም ቢሆን አትጨነቁ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋልና ይለናል ማቴ 6 ቁ28። የነገ ጭንቀት ማለት ወደፊትን የሚያጠቃልል ነው። ዛሬን ተጠንቅቃችሁ በቅድስና በፍጹም እምነት፤ በጸሎት ኑሩ የነገን የሚያውቅ አባት እርሱ ያስባል። ስለትላንትና ከማሰብ ይልቅ ዛሬን በአግባቡ እንያዘው።

ቅዱስ ጳውሎስ “በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥” ፊልጵስዩስ 3:13።

“ስለነገም መጨነቅ የለብንም፡ ነገ ገና አልመጣም፡ ነገ ይሄን አደርጋለሁ ይሄንን እሰራለሁ እያልንም በነገ መመካት የለብንም” ጠቢቡ ሰለሞን “ቀን የሚያመጣው ምን እንደሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ!” ምሳ 27፥1 ይላል።

አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር እኛም ዛሬ ስንጸልየው፤ “ጌታ የነገ እንጀራችንን ስጠን በሉ አይደለም ያለን ፤ የእለት እንጀራችንን በየእለቱ ስጠን ብለን ነው የምንጸልየው።

ሙሴ ምድረበዳ በነበረበት ጊዜ ለሕዝቡ ሲነግር፤ ጅግራ እና መና ስትለቅሙ ለዕለት የሚያስፈልጋችሁን ብቻ ልቀሙ ለነገ አዘጋጃለሁ ብሏል አላቸው።  አንዳንዶቹ ነገ አይታወቅም ብለው እምነቱን ተጠራጥረው አብዝተው ለቀሙና ሻገተ፤ ነገር ግን ነገም ዘነበ፤ እየተጠራጠሩ ይለቅሙ ነበር፡ እግዚአብሔርም ከሰማይ መና በየቀኑ ማውረዱን ቀጠለ የሰው ልጅም መጠራጠሩን ቀጠለ።

ፈጣሪ ለችግራችን መፍትሄ ያዘጋጃል፤   ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ፦ “ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” ማር 9፥23 የሚያምን ሰው ሁሉንም ማድረግ ይችላል። ጌታም ይህንን ሲያስረግጥልን፦ ሽክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ፤ ማዕበል ያናወጣችሁ ወደኔ ኑ “እኔ አሳርፋችኋለሁ፤ እንዲያውም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 23 ላይ እንዳለው፦ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል። ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና አልፈራም። ይላል። ይህን እምነት እንያዝ።

እግዚአብሔር በቃሉ የታመነ ነው። ይለናል ቅ. ጳውሎስ 10፡23።

 

 

Read More